ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከአንጎላ አልማዝ ማዕድን ማውጫ የወጣ መርዛማ ፈሳሽ በኮንጎ 12 ሰዎችን ገደለ
በአንጎላ ከአንድ ግዙፍ የአልማዝ ማዕድን ማውጫ በወጣ መርዛማ ፈሳሽ ቢያንስ 12 ሰዎች ሲሞቱ 4 ሺህ 500 መታመማቸውን የአጎራባቿ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሚኒስትር አስታውቀዋል።
ፈሳሹ የኮንጎ ወንዝ ገባር የሆነውን ወንዝ ወደ ቀይ ቀለም የቀየረው ሲሆን በርካታ ዓሳዎችን ገድሏል። አንዳንዶቹንም አሳዎች ነዋሪዎቹ መብላታቸውን የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ኢቭ ባዛይባ ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ አገራቸው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለደረሰባት ጉዳት ካሳ እንደምትፈልግ ቢገልፁም ምን ያህል እንደሆነ አልተናገሩም።
እስካሁን ድረስ መርዛማው ፈሳሽ ወጣበት ከተባለው የካቶካ ማዕድን ማውጫ ባለቤቶች ምንም ዓይነት ምላሽ አልተሰጠም።
ማዕድን ማውጫው የአንጎላን አልማዝ 75 በመቶ ያህሉን እንደሚያመርት ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
በሐምሌ ወር መጨረሻ ከማዕድን ማውጫ ውስጥ መርዛማ ተረፈ ምርቶችን የያዘ ማጠራቀሚያ መፍሰሱን ተከትሎ በዴሞክራቲክ ኮንጎ ድንበር ተሻግሮ የሚገኘው የሺሺፓ ወንዝ ወደ ቀይ ቀለም የተቀየረ ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ ጉማሬዎችን ፣ ዓሳዎችን እና ሌሎች እንስሳትን ገድሏል።
ሚኒስትሯ እንደሚሉት "በርካታ የሞቱ ዓሦች በወንዙ ላይ እየተንሳፈፉ ነበር። የመጀመሪያ ምላሽ የሚሆነውም ዓሳውን መውሰድ ነበር" ብለዋል።
የካሣይ ግዛት ባለስልጣናት የአካባቢው ነዋሪዎች ውሃ እንዳይጠጡ እና ከወንዙ ዓሳ እንዳይበሉ ቢያግዱም ነገር ግን ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተጎድተዋል ተብሏል።
በወንዙ ዳርቻ የሚኖሩ ማህበረሰቦች በተቅማጥ እና በሌሎች የጤና ችግሮች ተጎድተዋል።
ሚኒስትሯ እንደተናገሩት የአንጎላ መንግሥትም ሆነ የማዕድን ባለቤቱ ለተከሰተው ጉዳይ ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል ብለዋል።
ነገር ግን ላደረሱት "ብክለት" ይከፍላሉ ከማለት ውጭ አገራቸው ለጉዳቱ ሊከፈለኝ ይገባል የሚለውን ካሳ ተጨማሪ ዝርዝር አልሰጡም።
በአንጎላ መንግሥት ስር ያለው ኢንዲያማ ኩባንያ እና የሩሲያው አልሮሳ የጋራ ንብረት የሆነው ካቶካ ከውኃው ውስጥ ደለልን ለማጣራት ሁለት ግንባታዎችን መገንባቱንና የሚያፈሰወውም መታሸጉን ሮይተርስ ዘግቧል።