በሳዑዲ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን እንግልት የሚቃወም ሰልፍ ተካሄደ

ታትሟል

በሳዑዲ አረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ነው ያሉትን ግፍ የሚቃወሙ ሰልፈኞች አዲስ አበባ ከሚገኘው የአገሪቱ ኤምባሲ ውጪ በመገኘት ተቃውሟቸውን አሰሙ።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ሰልፈኞቹ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰው እስር፣ ግፍ እና መከራን የሳዑዲ መንግሥት እንዲያስቆም ጠይቀዋል።

በነዳጅ ዘይት ሐብት በበለጸገችው ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውን የሚገኙ ሲሆን በርካቶቹ ሕጋዊ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ የሌላቸው ናቸው በሚል በተለያዩ ጊዜያት እንግልትና እስር ሲገጥማቸው ቆይቷል።

አንዳንድ በሳዑዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በቅርብ ጊዜ እያጋጠማቸው ያለው እንግልት የተለየ እንደሆነና የመኖሪያና የመሥሪያ ሰነድ ያላቸውንም የሚጨምር እንደሆነ ተናግረዋል።

ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 17/2013 ዓ.ም በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የሳዑዲ መንግሥት በግዛቱ ውስጥ ባሉ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጸሙ የዘፈቀደ እስርና ሰቆቃዎችን ጨምሮ ሌሎች የጭካኔ ድርጊቶችን እንዲያስቆም አዲስ አበባ ለሚገኘው የአገሪቱ ኤምባሲ ጥሪ አቅርበዋል።

"እኔም ለወገኔ ድምፅ ነኝ" በሚል በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተገኙ ሰዎች በሳዑዲ በእስር ላይ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ላይ እየተፈጸመ ነው ያሉት የግፍ ድርጊት እንዲቆም ጠይቀዋል።

በተለያዩ ጊዜያት የሳዑዲ ጸጥታ ኃይሎች ሕገ ወጥ በሚሏቸው ስደተኞች ላይ በሚያካሂዱት አሰሳ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ እንደሚገኙ ይነገራል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎቹን ከሳዑዲ አረቢያ ወደ አገራቸው ለመመለስ እየጣረ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ስደተኞችን እንዲመለሱ አድርጓል።

በርካታ ኢትዮጵያውያን በጂቡቲና በሶማሊያ በኩል የተሻለ ሥራና ኑሮ ፍለጋ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ ለመግባት በሚያደርጉት ጥረት ባሕር ላይ ሰጥመው ለሞት መዳረጋቸው በተደጋጋሚ ተዘግቧል።

ተሳክቶላቸው ወደ የመን በመግባት በታጣቂዎችና በሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች አማካይነት ወደ ሳዑዲ ለመሻገር ቀላል የማይባል ገንዘብ ከፍለው ከባድ ችግር እንደሚገጥማቸው ይናገራሉ።

ቢቢሲ፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ቀደም ሲል ባወጧቸው ሪፖርቶች ላይ እንዳመለከቱት በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከድንበር አካባቢና ከተለያዩ የሳዑዲ ከተሞች ተይዘው በአሰቃቂ ሁኔታ በእስር ላይ ይገኛሉ።