ሳዑዲ አረቢያ የተከተቡ ሰዎች ወደ ግዛቷ ጉዞ እንዲያደርጉ ልትፈቅድ ነው

ሙስሊም ምዕመናን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ሳዑዲ አረቢያ ለኡምራ ጉዞ የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባትን የወሰዱ የውጭ አገር ዜጎች ወደ ቅዱሱ ከተማ መካ እንዲገቡ ልትፈቅድ ነው።

ይህንንም ተከትሎ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ሐይማኖታዊ ጉዞ ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎችን ጥያቄ መቀበል መጀመራቸው ተገልጿል።

የሳዑዲ አረቢያ ንጉሣዊ ግዛት በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት ከ18 ወራት በፊት አንስቶ ሁሉንም ድንበሮቿን ዘግታ ቆይታለች።

አሁን ግን እገዳዋን በማላላት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የተከተቡ የውጭ አገር ጎብኚዎች ወደ ግዛቷ እንዲገቡ መፍቀድ ጀምራለች።

ባለፈው ወር በነበረው የሐጅ ሥነ ሥርዓት ላይ የተሳታፊዎች ቁጥር በከፍተኛ ቁጥር እንዲቀንስ ተደርጎ 60 ሺህ ያህ ክትባት የወሰዱ የአገሪቱ ነዋሪዎች ብቻ እንዲገኙ ተደርጓል።

ወደ ሳዑዲ የሚደረገው የሐጅ ሐይማኖታዊ ጉዞ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ ሙስሊም በህይወት ዘመኑ ውስጥ ሊያደርገው የሚገባ ሐይማኖታዊ ተግባር ነው። ይህም በአመት አንድ ጊዜ ይደረጋል።

ሌላኛው ሐይማኖታዊ ጉዞ ዑምራ ግን በዓመቱ ውስጥ በየትኛውም ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን በዚህም ከዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ወደ ሳዑዲ ይጓዛሉ።

በሐይማኖታዊ ጉዞዎቹ ሙስሊም ምዕመናኑ ሁለቱን ቅዱስ ከተሞች መካና መዲናን ይጎበኛሉ።

የሳዑዲ መንግሥት ዜና ወኪል እንዳለው አገሪቱ ተጓዦች ወደ ግዛቷ ሲያቀኑ በመጀመሪያ ላይ በየወሩ 60 ሺህ ለሚደርሱ የተከተቡ ሰዎች ፈቃድ የሚሰጥ ሲሆን ቀስ በቀስ ቁጥሩ እያደገ አስከ ሁለት ሚሊየን እንደሚደርስ ተገልጿል።

ሳዑዲ የተከተቡ ተጓዦች ወደ ግዛቷ እንዲገቡ ስትፈቅድ እውቅና የሰጠቻቸው የኮሮናቫይረስ ክትባቶችንም ዘርዝራለች። በዚህም መሠረት ፋይዘር/ባዮንቴክ፣ ኦክስፎርድ-አስትራዜኒካ እና ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን መሆናቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም ከውጭ አገራት የሚመጡ ጎብኚዎች አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ መሆን ይጠቅባቸዋል መባሉን ዜና ወኪሊ የሐጅ ሚኒስትሩን አብዱልፋታህ ቢን ሱሌይማን ማሻትን ጠቅሶ ዘግቧል።

አስካሁን ድረስ በሳዑዲ አረቢያ 532,000 ያህል በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተነገረ ሲሆን ከ8,300 በላይ ሰዎች ደግሞ ለህልፈት ተዳርገዋል።