ሜክሲኮ በሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር የአሜሪካ ጦር መሣሪያ አምራቾችን ከሰሰች

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሜክሲኮ መንግሥት በአገሪቱ ለሚከሰቱ ደም አፋሳሽ ግጭቶች የአሜሪካ ግዙፍ የጦር መሣሪያ አምራቾችን ከሰሰ።
የሜክሲኮ መንግሥት ጦር መሣሪያ አምራች ኩባንያዎቹ የንግድ ስርዓታቸው ቸልተኛ በመሆኑ ለደም አፋሳሽ ግጭቶች አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ይላል።
ከዚህ በተጨማሪም ኩባንያዎቹ የጦር መሣሪያ ሽያጫቸው በሜክሲኮ የሕገ ወጥ ጦር መሣሪያ ዝውውር እንዲኖር እና በዚህም በርካቶች ሕይወታቸውን እንዲያጡ ሆኗል ይላል የሜክሲኮ መንግሥት።
የሜክሲኮ መንግሥት በከፈተው ክስ ኩባንያዎቹ 10 ቢሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍሉት ጠይቋል።
ክስ ከተመሰረተባቸው ጦር መሣሪያ አምራች ኩባንያዎች መካከል ስሚዝ ንድ ዌሰን እንዲሁም ባሬት ፍየርአርምስ ይገኙበታል።
የሜክሲኮ መንግሥት ክሱን በአሜሪካዋ ማሳቹሴት ግዛት የከፈተ ሲሆን፤ ኩባንያዎቹ በጉዳዩ ላይ እስካሁን ያሉት ነገር የለም።
የጦር መሣሪያ አምራቾቹ "ምርቶቻቸው በሕገ ወጥ መንገድ እንደሚዘዋወሩ እና ለሕገ ወጥ ተግባራት እንደሚውሉ ያውቃሉ" ይላል የሜክሲኮ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ዶሴ።
ሜክሲኮ የጦር መሣሪያ ሽያጭን በተመለከተ ጠንካራ ሕግ ያላት ሲሆን፤ በሜክሲኮ የጦር መሣሪያ መግዛት የሚቻለው በመዲናዋ ከሚገኝ አንድ የጦር ካምፕ ብቻ ነው።
እንደ ሜክሲኮ መንግሥት መግለጫ ከሆነ በሜክሲኮ የሚገኙ ወንጀለኛ ቡድኖች የአሜሪካ ኩባንያዎች ያመረቷቸውን በሺዎች ሚቆጠሩ የተለያዩ አይነት የጦር መሣሪያዎችን እና ጥይቶችን ይገዛሉ።
የወንጀል ቡድኖቹ የጦር መሣሪያዎቹን አሜሪካ ከሚገኙ የሸቀጥ መሸጫ መደብሮች እና ከኢንተርኔት ገዝተው በሜክሲኮ ለሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ተግባራት ያውላሉ።
የሜክሲኮ መንግሥት እንደሚለው እአአ ከ2014 እስከ 2018 ባሉት አራት ዓመታት በሜክሲኮ ከተያዙ ጦር መሣሪያዎች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ከአሜሪካ ወደ ሜክሲኮ የገቡ ናቸው ብሏል።
እአአ በ2019 ብቻ በሜክሲኮ ለተመዘገቡ ከ17 ሺህ በላይ ግድያዎች በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የገቡ የጦር መሣሪያዎች ምክንያት ናቸው ተብሏል።
የሜክሲኮ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማርሴሎ ኤብራርድ ፤ "ይህን ክስ እናሸንፋል። ወደ ሜክሲኮ የሚገቡ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ነው የምቀንሰው" ብለዋል።














