በኬኒያ ነዳጅ የጫነ ተሽከርካሪ ፈንድቶ 13 ሰዎችን ለህልፈት ዳረገ

አደጋው የተከሰተብት ሥፍራ ሰዎች ተሰባስበው

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በምዕራብ ኬንያ አንድ ነዳጅ የጫነ ተሽከርካሪ ተገልብጦ በተከሰተ ፍንዳታ ቢያንስ የ13 ሰዎች ሕይወት አለፈ።

መኪናው ቅዳሜ ምሽት ላይ ኪሱሙ እና ቡሲያ ከተሞች መካከል ላይ ወተት ጭኖ ሲሄድ ከነበረ ሌላ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ ነው አደጋው የተከሰተው።

የዐይን እማኞች በአደጋው ወቅት የነበረውን ትዕይንት "ግዙፍ የእሳት ኳስ" ሲሉ ገልጸውታል።

መኪናው ከመፈንዳቱ በፊት ነዋሪዎች ጀሪካን በመያዝ የሚፈሰውን ነዳጅ ለመቅዳት ወደ መኪናው ተጥግተው ነበር ተብሏል።

አንድ የአካባቢው የፖሊስ አዛዥ 24 ሰዎች በደረሰባቸው ከባድ ቃጠሎ ምክንያት ሆስፒታል ገብተው እየታከሙ እንዳሉ ገልጸው፤ ከተጎዱት መካከል ህጻናት እንደሚገኙበትም አክለዋል።

መርማሪዎች አሁንም ፍንዳታው በተከሰተበት ቦታ ላይ ፍለጋዎችን እያካሄዱ ሲሆን፤ የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

"አጥንቶች በተገኙበት ቦታ ላይ ሙሉ በሙሉ የተቃጠሉ ሰዎች ከነበሩ ለማወቅ እና ለመለየት በአግባቡ ምርመራ ያስፈልጋል" ሲሉ የአካባቢው የፖሊስ ኃላፊ ቻርልስ ቻቻ ተናግረዋል።

የእሳት አደጋ ሰራተኞች ከዋና ከተማው ናይሮቢ በስተሰሜን-ምዕራብ 320 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው የማላንጋ ከተማ አካባቢ ለመድረስ ሁለት ሰዓታት ነበር የፈጀባቸው።

አደጋው ከደረሰበት ቦታ አቅራቢያ በርካታ ሞተር ብስክሌቶች እየተቃጠሉ መገኘታቸውንም የዐይን እማኞቹ ጨምረው ገልጸዋል።

ከአደጋው ከተረፉት መካከል አንዱ የሆኑት ዋይክሊፍ ኦቲኤኖ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ነዳጅ በጫነው መኪና ዙሪያ ጀሪካን ይዘው ለመቅዳት ሲቀርቡ ነበር በእሳት መቀጣጠል የጀመረው።

"ራሴን ለማትረፍ መሮጥ ችያለሁ ። ምን ያህል ዕድለኛ እንደሆንኩ አላውቅም፤ ምክንያቱም አብሬያቸው የነበርኩ ሰዎች እንዳልተረፉ ሰምቻለሁ" ብለዋል ዋይክሊፍ።

የቢቢሲዋ ሜርሲ ጁማ እንደምትለውም በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የመንገድ ላይ አደጋዎች አዲስ ነገር አይደሉም። የጭነት መኪኖች እና ሌሎች ተሽከርካሪዎች ጭነት ይዘውም በፍጥነት ይጓዛሉ - አንዳንዴ በምሽትም ጭምር።

በኬንያ በየዓመቱ ወደ 3,000 የሚጠጉ ሰዎች በመኪና አደጋ ይሞታሉ።