እንደ ፎጣ በሳጥን ተጠቅልለው በአውሮፕላን ከጃፓን ያመለጡት የኒሳን መኪና ሥራ አስኪያጅ

ካርሎስ ጎሰን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ሚስተር ካርሎስን ቢቢሲ ጠየቃቸው፡፡ እንደ ዕቃ በሳጥን ውስጥ ታሽጎ መሄድ አይጨንቅም?

ካርሎስ መለሱ፡፡ በሕይወቴ ረዥሙ ጊዜ የምለው መቼ እንደሆነ ታውቃለህ? በሳጥን ውስጥ ታሽጌ አውሮፕላን ውስጥ ከገባሁ በኋላ ነው፡፡

አውሮፕላኑ እስኪነሳ የነበሩት 30 ደቂቃዎች የሕይወቴ ረዥምና አስጨናቂ ጊዜዎች ናቸው፡፡ እንዲህ ያለ ረዥም ሰዓት በሕይወቴ አሳልፌ አላውቅም፡፡"

በነሐሴ 2019 እኩለ ሌሊት ከመድረሱ በፊት የኒሳን መኪና ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ሳጥን ውስጥ እየታሸጉ ነበር፡፡

ሳጥኑ ካርጎ ውስጥ የሚጫን ነው፡፡ በፕላስተር ጥፍንግ ተደርጎ ታሰረ፡፡ ይህ ሳጥን ብዙውን ጊዜ የሙዚቃ መሣሪያዎች ተጭነው የሚወሰዱበት ጠባብ ሳጥን ነው፡፡

ሰውዬው እንዴት በዚህ ሳጥን ውስጥ ኩርምት ብለው መግባት እንዳቻሉ እንጃ፡፡

አውሮፕላኑ የሚነሳው ከጃፓን ነው፡፡ ከቶኪዮ ወጣ ብሎ ከሚገኝ አውሮፕላን ጣቢያ፡፡

አውሮፕላኑ መነሻ ሰዓት ልክ ከምሽቱ 5፡00 ሰዓት ነው፡፡

ካርሎስ በጃፓን ማንም ያውቃቸዋል፡፡ ምናልባትም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥሎ በደንብ የሚታወቀው ፊት የርሳቸው ነው፡፡ የኒሳን መኪና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ የኒሳን ብቻ ሳይሆን የፈረንሳዩ ሬኖ መኪና ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅም ነበሩ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት በፖለቲካ አሻጥር እስር ተፈረደባቸው፡፡ ዓመታዊ ደመወዝህን ዋሽተሃል ተብለው በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡ በዚያ ወቅት የኒሳን፣ የሬኖና ሚስቲቡሺ መኪናዎች ጥምረት የሆነው ድርጅት ሥራ አስኪያጅም ነበሩ፡፡

በፖለቲካ አሻጥር የጃፓን መንግሥት ሊያስረኝ ፈለገ ይላሉ፡፡ እያመለጡ ያሉትም ለዚሁ ነው፡፡

ሚስተር ካርሎስ ወጪ ቀንሰው ኒሳን መኪናን ትርፋማ አድርገውታል፡፡ የፈረንሳዩ ሬኖ መኪና የኒሳንን 45 ከመቶ ድርሻ እንዲወስድም አስችለው ነበር፡፡ አሁንም የኒሳን ግማሽ ባለቤትነት ሬኖ እንደያዘው ነው ያለው፡፡

ብቻ ለማንኛውም ሚስተር ካርሎስ እስር ቤት ከመበስበስ ማምለጥን ፈለጉ፡፡

በዜግነት ሊባኖሳዊ ናቸው፡፡ ለመሸሽ እየሞከሩ ያሉትም ወደ ሊባኖስ ነው፡፡

በጃፓን አገር እጅግ የተከበሩና ገናና ስም ያላቸው ሚስተር ካርሎስን በአንድ ሳጥን ውስጥ ተጠቅልለው ገብተው ያመልጣሉ ያለ ማን ነበር?

እርግጥ ነው ከዚያ በፊት ለአንድ ዓመት በቁም እስርና በመደበኛ እስር ፍዳቸውን በልተው ወጥተዋል፡፡

ቢሆንም እኒህ የታፈሩና የተከበሩ ሰው በቁምሳጥን ታሽገው ይወጣሉ ማን አለ?

ዓመት እስር ጠጥተው የወጡት ሚስተር ካርሎስ የክስ ፋይላቸው አልተዘጋም፡፡

መቼ ተነካና፡፡ በዋስ ነበር የተፈቱት፡፡ የክስ ሂደቱ ለዓመታት ሊጓተት ይችላል፡፡

እሱ ብቻ አይደለም ያስፈራቸው፡፡ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ 15 ዓመታትን በእስር ይማቅቃሉ፡፡ በጃፓን ደግሞ ተጠርጣሪ ጥፋተኛ የመባሉ ምጣኔ ከመቶ 99.4 እጅ ነው፡፡

የሙዚቃ መሳሪያ ማስቀመጫ ሳጥን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ካርሎስ ወሰኑ፡፡

15 ዓመት ከመማቀቅ ለምን 15 ሰዓታትን የሞት ሽረት ትግል አላደርግም ብለው ቆረጡ፡፡ ለነገሩ 15 ሰዓታትን የሚወስድም አይደለም፡፡ ከጃፓን ቶኪዮ እስከ ሊባኖስ ቤይሩት የስንት ሰዓት በረራ ነው?

አስጨናቂው እኮ በረራው አይደለም ይላሉ፤ ካርሎስ፡፡ አስጨናቂው ከበረራ በፊት ያለው ፍተሻ ነው፡፡ አስጨናቂውና ከ15 ዓመታት የእስር ሕይወት የማይተናነሰው ሰቀቀን ያለው አውሮፕላኑ እስኪነሳ ያለው ጊዜ ነው፡፡

የመኪኖች ጌታ፣ የኒሳን አባት ካርሎስ የመጨረሻ ሰዓት

ዝነኛው ካርሎስ በቁም እስር ላይ ሳሉ ከሚወዷት ሚስታቸው ካሮል ጋር ምንም መገናኘት እንደማይችሉ ተነገራቸው፡፡

በዚህ ጊዜ ነው አንድ በትክክል አንድ ጀብዱ መፈጸም እንዳለባቸው ራሳቸውን ያሳመኑት፡፡

ችግር የሆነብኝ ይሄ መከረኛ ፊቴ ነው ይላሉ፡፡ የካርሎስ ፊት ዕውቅ ፊት ነው፡፡ ማንም ጃፓናዊ ይለየዋል፡፡ ዝነኛ የመሆን ጣጣው ይህ ነው፡፡

ታዲያ ይህን ፊት ይዘው እንዴት ሊሾልኩ ይችላሉ፡፡

‹‹ለማምለጥ ከፈለኩ ሻንጣ ውስጥ ሊቆለፍብኝ ይገባል፡፡ ወይም ሻንጣ የሚመስል ሳጥን ውስጥ፡፡ ሌላ አማራጭ አልነበረም››

ሻንጣ ወይስ ሳጥን እያሉ ማማረጥ ጀመሩ፡፡ ሳጥን ወይስ ሻንጣ፣ ሻንጣ ወይስ ሳጥን ?

ሳጥን ይሻላል፡፡ ለምን?

‹‹ምክንያቱም ያን ወቅት በጃፓን በርካታ የሙዚቃ ኮንሰርቶች የሚካሄዱት ጊዜ ነበር፡፡ በርካታ ሙዚቀኞች ጊታራቸውን፣ ከበሯቸውን ወዘተ የሚያስቀምጡበት ሳጥን አለ፡፡ ያ ሳጥን እኔን ጠቅልሎ ማስገባት ይችላል፡፡ እሱ የተሻለ ሆነ ተሰማኝ፡፡››

ቀጥሎ የመጣው ፈተና በቁም እስር ላይ የነበረ ሰው እስከ አውሮፕላን ጣቢያ እንዴት ተደብቆ ማምለጥ ይችላል የሚለው ነው፡፡

ሚስተር ካርሎስ ዕድሜ ዘመናቸውን በውድ ሱፍ ተሸቆጥቁጠው ነው የኖሩት፡፡ አንደኛ ሀብታም ናቸው፡፡ ሁለተኛ ሥመ ጥር ናቸው፡፡ በጃፓን አይደለም በተቀረውም ዓለም ማንም ያውቃቸዋል፡፡

ስለዚህ ራሳቸውን መለወጥ ነበረባቸው፡፡ ተራ ጁንስና ቲሸርት ለበሱ፡፡ ከአሮጌ ተራ የገዙትን ጂንስና ቲሸርት ግጥም አድርገው ለበሱና የማይደፈረውን ደፈሩ፡፡

ከዚያ በኋላ ዋናው ድራማ ተጀመረ፡፡

ከመኖርያቸው ቶኪዮ ተነስተው እንደ አውሎንፋስ በሚንደረደረው ቡሌትባቡር ወደ ኦሳካ ሄዱ፡፡ እዚያ አውሮፕላን ጣቢያ አለ፡፡ አውሮፕላን ጣቢያው ውስጥ አንድ የግል ጄት ቆሞ ይጠብቃቸዋል፡፡

ጄቱ ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ግን አንድ በአቅራቢያ የሚገኝ ሆቴል መሄድ አለባቸው፡፡

እዚያ ነው የሳቸው ሻንጣ ያለው፡፡ እዚያ ነው የሳቸው ሳጥን ያለው፡፡ ልብስ መያዣቸው ግን አይደለም፡፡ እሳቸው እንደ ፎጣ ተጠቅልለው የሚገቡት ሳጥን እንጂ፡፡

‹‹ሳጥን ውስጥ ተኮማትረህ አንድ ጊዜ ከገባህ በኋላ ስለ ድሮም ስለወደፊትም ማሰብ ታቆማለህ፡፡ የምታስበው ስለዚያች ቅጽበት ብቻ ነው›› ብለዋል ለቢቢሲ፡፡

ሚስተር ካርሎስ እዚያ ሆቴል ሲገቡ እንጂ ሲወጡ አልታዩም፡፡ ሚስተር ካርሎስ ከገቡበት ሆቴል ሌሎች ሁለት ሰዎች (አባትና ልጅ) ሻንጣና ሌላ የሙዚቃ መሣሪያ ማስቀመጫ ሳጥን ተሸክመው ሲወጡ ግን ታይተዋል፡፡

እኒህ አባትና ልጅ ማይክል እና ፒተር ቴይለር ይባላሉ፡፡ ሙዚቀኛ ነን ብለው ነው አውሮፕላን የሚሳፈሩት፡፡

እውቅ ሙዚቀኛ ነን ብለው ነው ጄት የሚያበሩት፡፡

‹‹በጠቅላላው ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል ሳጥን ውስጥ እንደቆየሁ ነው የምገምተው፡፡ ነገር ግን አንድ ዓመት ተኩል የቆየሁ ያህል ነው የተሰማኝ›› ብለዋል ካርሎስ፡፡

የሆነው ሆኖ የግል ጄቱ በሰዓቱ ተነስቶ እንዲበር ተፈቀደለት፡፡ ሌሊቱን ሙሉ በረረ፡፡ መጀመርያ ቱርክ አረፈ፡፡ ከዚያ በጠዋት በሌላ አውሮፕላን ሳጥኑ ወደ ሊባኖስ በረረ፡፡

ራሳቸውን እንደ ሙዚቀኛ አስመሰለው ሚስተር ካርሎስን እንደ ፎጣ በሳጥን አጣጥፈው ጠቅልለው በግል ጄት ያስመለጡት ማይክል ቴይለርና ልጁ ፒተር ቴይለር በገዛ አገራቸው አሜሪካ ለጃፓን ተላልፈው ተሰጥተዋል፡፡

ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸውም 3 ዓመት እስር ይጠብቃቸዋል፡፡

የኒሳን፣ የሬኖ እና የሚስቲቡሺው ጌታ ሚስተር ካርሎስ ግን በትውልድ አገራቸው ሊባኖስ ታፍረውና ተከብረው ኑሯቸውን ቀጥለዋል፡፡

እንደ ፎጣ ተጠቅልለው የመጡባት ቁም ሳጥን፣ ሕይወታቸውን የታደገችው ቁምሳጥን የት ይሆን ያለችው?