ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢራን የኑክሌር ስምምነት፡ አዲሱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኢራንን አስጠነቀቁ
የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብርን ለመገደብ የሚያስችለውን ልዩ ስምምነት ለማደስ ድርድሩ እየቀጠለ ባለበት ወቅት አሜሪካ እና አጋሮቿ በተደቀነው ስጋት "መንቃት" አለባቸው ሲሉ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጥሪ አቅርበዋል።
ናፍታሊ ቤኔት በኢራን "በጭካኔ ሰው የሚሰቅለው አገዛዝ" የኒውክሌር መሣሪያን ይፈልጋል ቢሉም ኢራን በተደጋጋሚ አስተባብላለች።
ዲፕሎማቶች ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥለው የወጡትን ስምምነት ለማደስ እርምጃ መኖሩን ገልጸው ክፍተት ያላቸው ጉዳዮች መኖራቸው ታውቋል።
እስራኤል ስምምነቱን አጥብቃ ትቃወማለች።
ኢራን አርብ ዕለት በወግ አጥባቂ አመለካከቶቻቸው የሚታወቁትን የአገሪቱን ከፍተኛ ዳኛ ኢብራሂም ራይሲን አዲስ ፕሬዝዳንት አድርጋ መርጣለች። ምርጫውም ለራይስ ያደላ ነበር ተብሎ በብዙዎች ታይቷል።
የተመራጩ ፕሬዝዳንት በነሐሴ ወር በዓለ ሲመታቸው የሚፈጸም ሲሆን አሜሪካ ማዕቀብ ከጣለችባቸው መካከልም ይጠቀሳሉ። ከዚህ ቀደም የፖለቲካ እስረኞችን ከመገደል ጋር ስማቸው ተደጋገግሞ ይነሳል።
ከስድስቱ የተደራደሩ አገራት (አሜሪካ፣ ዩኬ፣ ፈረንሳይ፣ ቻይና፣ ሩሲያ እና ጀርመን) ተደራዳሪዎች እና በኢራን መካከል ከሚያዝያ ጀምሮ ስምምነቱን ለማደስ ድርድር ነው። ኢራን የኒውክሌር እንቅስቃሴዋን በመገደብ የማዕቀብ እፎይታን ለማግኘት እየተሠራ ነው፡፡
አሜሪካን በተናጠል ከለቀቀች በኋላ ኢራን ስምምነቱን በተደጋጋሚ እየጣሰች ነው።
እሁድ አገራቱ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በተካሄደው ቀጥተኛ ላልሆነው ድርድር በቪየና ለስድስተኛ ዙር ተሰብስበው የነበረ ቢሆንም ልዑካኑ ወደ አገራቸው ተመልሰው ውይይቱ እንዲዘገይ ተደርጓል።
የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ ለመንግሥታዊው ቴሌቪዥን ተደራዳሪዎቹ ለስምምነት "ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አሁን ቀርበዋል" ብለዋል። ሆኖም በመካከላቸው ያለውን ክፍተት መሙላት ግን "ቀላል ሥራ አይደለም" ሲሉ ገልጸዋል።
የአውሮፓ ሕብረት መልዕክተኛ የሆኑት ኤንሪኬ ሞራም በተመሳሳይ በቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ የተፈጠረው መሻሻል የበለጠ ግልጽነት እንደሰጣቸው በመጥቀስ የፖለቲካ ችግሮች ምን እንደሆኑ ግልፅ ሃሳብ እንደሰጣቸው ገልጸዋል።
የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን ማዕቀብን ጨምሮ ኢራን ልታደርጋቸው በገባችው ቃል "ለመጓዝ አሁንም ርቀት አለ" ብለዋል።
ምንም እንኳን የኒውክለር መሣሪያዎችን ለመሥራት በሚያስፈልገው ደረጃ ለመድረስ ገና ቢቀራትም ኢራን ዩራንየምን በከፍተኛ ደረጃ እያበለጸገች ትገኛለች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቀደም ሲል እንደተናገሩት ቀጥተኛ ያልሆነው ድርድር ራይሲ ስልጣን ከያዙ በኋላም ይቀጥላል።
እስራኤል ስምምነቱን ለምን ትቃወማለች?
ኢራን እና እስራኤል ለረጅም ጊዜ የዘለቀ "የማይታይ ጦርነት" ውስጥ የገቡ ሲሆን ይህም ሁለቱም ሀገሮች አንዱ ያደረገውን ሌላው በሚያደርገው ድርጊቶች እንዲሳተፉ ቢያደርጋቸውም ወደ ሁሉን አቀፍ ግጭትን ግን አላመሩም።
የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ ካሜኒ የእስራኤል መንግስት እንዲወገድ ደጋግመው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ እአአ በ 2018 አገሪቱን ከክልሉ መወገድ ያለባት "የካንሰር ነቀርሳ" እንደሆነች ገልፀዋል።
ኢራንን እንደ ዋንኛ ስጋት የምትመለተው እስራኤል የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን ማልማት እንደምትፈልግ ደጋግማ አስታውቃለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኔት ለካቢኔያቸው "የዓለም ኃያላን እንዲነቁ እና ከማን ጋር አብረው እንደሚሠሩ ለመገንዘብ የመጨረሻው ዕድል ነው" ብለዋል።
"በጭካኔ ሰው የሚሰቅል ገዢዎች የጅምላ ገዳይ መሳሪያዎች እንዲኖሩት በጭራሽ ሊፈቀድለት አይገባም።"
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ጠብ እንደገና አገርሽቷል። እስራኤልን ባለፈው ዓመት በከፍተኛ የኒውክሌር ሳይንቲሷ በመግደል እና በሚያዝያ ደግሞ በአንዱ የዩራኒየም ማበልፀጸጊያዋ ላይ ጥቃት በመሰንዘር እስራኤልን ትከሳለች።