ቶኪዮ ኦሎምፒክ፡ ኡጋንዳዊው የኦሊምፒክ ተወዳዳሪ በጃፓን ኮሮናቫይረስ እንዳለበት በምርመራ ተረጋገጠ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኡጋንዳ የኦሊምፒክ ቡድን አባል የሆነ አንድ አትሌት ወደ ጃፓን ሲገባ በተደረገለት ምርመራ የኮሮናቫይረስ የተገኘበት የመጀመሪያው የኦሊምፒክ ልኡክ አባል ሆኗል።
ሐምሌ 16 ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው የኦሊምፒክ ጨዋታ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ካለፈው ዓመት የተዘዋወረ ሲሆን በጃፓን አዲስ የቫይረሱ የስርጭት ማዕበል ቢከሰትም ጨዋታው ይካሄዳል።
ኡጋንዳም የቫይረሱ ስርጭት እጅግ መጨመሩን ተከትሎ መንግሥት ባለፈው አርብ የእንቅስቃሴ ገደቦችን አድርጋለች።
ስሙ ያልተጠቀሰው ኡጋንዳዊም ሙሉ ክትባት ከወሰዱ ዘጠኝ የቡድኑ አባላት ውስጥ መሆኑንም ዘገባዎች አመልክተዋል።
ቦክሰኞችን፣ አሰልጣኞችን እና የመንግሥት ባለሥልጣናትን ያካተተው ቡድን ከኡጋንዳ ከመነሳቱ በፊት ከኮሮናቫይረስ ነፃ መሆኑን አረጋግጦ ነበር።
ሆኖም ከመካከላቸው አንድ ሰው ቅዳሜ ዕለት ቶኪዮ ናሪታ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ በተደረገለት ምርመራ ቫይረሱ ስለተገኘበት በመንግሥት በተዘጋጀ ለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲገባ መደረጉን የጃፓን ባለሥልጣናት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልፀዋል።
የተቀሩት የቡድኑ አባላት ከጨዋታዎች በፊት ስልጠና ወደ ሚወስዱበት በምዕራብ ጃፓን ወደ ምትገኘው ኦሳካ ለግላቸው በተመደበ አውቶብስ መሄዳቸውም ታውቋል።
የኡጋንዳው ልኡክ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከመጀመራቸው በፊት ለስልጠና ወደ ጃፓን የገቡት ሁለተኛው የውጭ አትሌቶች ቡድን ሲሆን ቀዳሚው የአውስትራሊያ የሴቶች የሶፍትቦል ቡድን ነበር።
ከውጭ አገር የሚመጡ ተመልካቾች በጃፓኑ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ እንዳይታደሙ ክልከላ የተደረገ ሲሆን የአገር ውስጥ ተመልካቾችን የተመለከተው ውሳኔም ሰኞ ለት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።












