ኮሮናቫይረስ፡ ተቃዋሚዎች በብራዚል ለተከሰተው የኮቪድ ቀውስ ፕሬዚደንት ቦልሶናሮን ተጠያቂ አደረጉ

በብራሲሊያ ተቃዋሚዎች በፕላስቲክ የተሠራ የፕሬዚንደቱን አምሳያ አሻንጉሊት ይዘው ታይተዋል።

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, በብራሲሊያ ተቃዋሚዎች በፕላስቲክ የተሠራ የፕሬዚንደቱን አምሳያ አሻንጉሊት ይዘው ታይተዋል
ታትሟል

የብራዚል ፕሬዚደንት ጀር ቦልሶናሮ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሰጡትን ምላሽ በመቃወም በአገሪቷ ተቃውሞ ተካሄደ።

በዋና መዲናዋ ብራዚሊያ በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በምክር ቤቱ ፊት ለፊት በመሰባሰብ ፕሬዚደንቱ ከሥልጣናቸው እንዲለቁ እና ተጨማሪ ክትባት እንዲቀርብላቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ተቃውሞው ሪዮ ዲ ጀኔሮን ጨምሮ በሌሎች በርካታ ዋና ዋና ከተሞች እየተካሄደ ነው።

የፕሬዚደንት ቦልሶናሮ የሕዝብ ድጋፍ ለወረርሽኙ በሰጡት ምላሽ ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።

ብራዚል በኮሮናቫይረስ ሳቢያ እስካሁን ወደ 460 ሺህ የሚጠጋ ሞት መዝግባለች። ይህም በዓለማችን በሟቾች ቁጥር አሜሪካን በመከተል ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል።

በበሽታው በተያዙ ሰዎች ቁጥርም ከ16 ሚሊዮን በላይ በመመዝገብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

የብራዚል ምክር ቤት መንግሥት ወረርሽኙን የተቆጣጠረበትን መንገድና ዘገምተኛ በሆነው የክትባት ፕሮግራም ላይ ምርመራ እያካሄደ ነው።

ቅዳሜ ዕለት የተካሄደው ተቃውሞም በፕሬዚደንቱ ላይ ተጨማሪ ጫና ይፈጥራል ተብሏል።

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ፣ የንግድ ማኅበራት እና ማኅበራዊ ንቅናቄዎች የክትባት ፕሮግራሙን እንዲቆም በማድረጋቸው እና የሚመጣው መዘዝ ችላ በማለት ቦልሶናሮን ከሰዋል።

በአገሪቷ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው በቫይረሱ መያዙ የአገሪቷን የጤና ሥርዓት ለውድቀት ዳርጎታል።

የፋር ራይት መሪው ቦልሶናሮ "የእንቅስቃሴ ገደቡ የሚያስከትለው ኢኮኖሚ ቀውስ ቫይረሱ ጥሎት ከሚያልፈው የባሰ ይሆናል" በሚል በተደጋጋሚ የእንቅስቃሴ ገደብ እርምጃን ሲቃወሙ ነበር።

በብራሲሊያ ተቃዋሚዎች በፕላስቲክ የተሠራ የፕሬዚንደቱን አምሳያ አሻንጉሊት ይዘው ታይተዋል። ተቃዋሚዎቹ በያዟቸው መፈክሮችም ፕሬዚደንቱ ከሥልጣናቸው እንዲባረሩ፣ ተጨማሪ ክትባት እንዲያገኙ እና የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

በብራዚል ላሉ ቀደምት ህዝቦች የተሻለ ጥበቃ እንዲደረግላቸው እና በአማዞን የሚደረገው የደን ጭፍጨፋ እንዲቆምም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በሪዮ ዲ ጀኔሮ የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, በሪዮ ዲ ጀኔሮ በርካቶች የተሳተፉበት ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ተካሂዷል

በሪሲፍ ከተማ ፖሊስ በተቃዋሚዎች ላይ የጎማ ጥይቶችንና አስለቃሽ ጭስ መተኮሳቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

በአንዳንድ ከተሞች ደግሞ በወረርሽኙ የሞቱትን ሰዎች አስበዋል።

ሐሙስ ዕለት የብራዚል የሥነ ሕይወት የጥናትና ምርምር ማዕከል-ቡታንታን ኢንስቲትዩት ለምክርቤት ኮሚቴ የክትባቱን ፕሮግራም የቦልሶናሮ እርምጃ ዘገምተኛ አድርጎታል ማለቱን የስፔን የዜና ወኪል ዘግቧል።

የተቋሙ ዳሬክተር ዶክተር ዲማስ ኮቫስ እንዳሉት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ቡታንታን 100 ሚሊየን ዶዝ 'ኮሮናቫክ' ክትባት ለመንግሥት ለማቅረብ ሃሳብ አቅርቦ ነበር።

ክትባቱ ከቻይናው ሲኖቫክ ባገኘው ፈቃድ በተቋሙ የሚመረት ነው።

እቅዱ የመጀመሪያውን 5 ሚሊየን ክትባት በታኅሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ማቅረብን ያካተተ እንደነበር ዶክተር ዲማስ ተናግረዋል።

ይሁን እንጅ ፕሬዚደንት ቦልሶናሮ መንግሥታቸው የቻይናን ክትባት በፍፁም እንደማይገዛ ቃል መግባታቸውን ዶክተር ዲማስ አክለዋል።

"እቅዱ ተቀባይነት ቢያገኝ ክትባቱን በመውሰድ የዓለማችን ቀዳሚ አገር እንሆን ነበር " ብለዋል ዶክተር ዲማስ ለኮሚቴው።

ተቋሙ በዚህ ዓመት መጋቢት መጨረሻ ድረስ 100 ሚሊየን ዶዝ ክትባት ማቅረብ ይችልም እንደነበርም ዶ/ር ዲማስ አስረድተዋል።

ብራዚል እስካሁን 46 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት ነው ያገኘችው። ሁለቱን ዶዝ ክትባት የወሰዱትም 10 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው።

ቀደም ብሎ በላቲን አሜሪካ የፋይዘር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካርሎስ ሙሪሎ ለምክር ቤቱ ኮሚቴ የቦልሶናሮ መንግሥት ባለፈው ታኅሳስ ወር ከአሜሪካው የመድሃኒት አምራች ድርጅት ለቀረበለት 1.5 ሚሊየን ዶዝ ክትባትም ምላሽ እንዳልሰጠ ተናግረዋል።