በዴሞክራቲክ ኮንጎ የፈነዳው እሳተ ገሞራ በርካቶችን ያለመጠለያ አስቀረ

ኮንጎ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እሳተ ገሞራ መፈንዳቱን ተክትሎ ብዙዎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል። ነዋሪዎች ጥለውት ወደሄዱት ቤታቸው በመመለስም የጠፉ የቤተሰብ አባላቶቻቸውን እየፈለጉ ይገኛ።

ባለፍነው ቅዳሜ ነበር የኒራጎንጎ ተራራ በእሳተ ገሞራ የቀለጠ አለት ልክ እንደ ወንዝ ወደ ነዋሪዎች ቤት የፈሰሰው። ነገር ግን በደቡባዊ ኮንጎ ወደምትገኘው እና የሁለት ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ ወደሆነችው የጎማ ከተማ ሳይደርስ ቆሟል።

እስካሁን ቢያንስ 15 ሰዎች መሞታቸው የተረጋገጠ ቢሆንም የአገሪቱ ባለሥልጣኖች ነዋሪዎች በከፋ ሁኔታ ወደሚገኙባቸው አካባቢዎች በመሄድ አሰሳ እያደረጉ በመሆኑ ቁጥሩ ሊጨምር ይችላል።

ከተጎጂዎቹ መካከል ዘጠኙ ከእሳተ ገሞራው ሲሸሹ በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ናቸው።

ሌሎች አራት ሰዎች ከእስር ቤት ለማምለጥ ሲሞክሩ ሲገደሉ ሁለት ሰዎች በእሳት ተቃጥለው መሞታቸውን የመንግሥት ቃል አቀባይ ፓትሪክ ሙያያ እሁድ ዕለት ተናግረዋል።

ከ170 በላይ ሕፃናት ሳይጠፉ እንዳልቀሩ እና ሌሎች 150 የሚሆኑ ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው መለያየታቸወን የዩኒሴፍ መረጃ አመልክቷል። ከወላጆቻቸው የተነጠሉ ታዳጊዎችን ለመርዳትም የመጠለያ ማዕከላት ይቋቋማሉ ብሏል ተቋሙ።

እሳተ ገሞራው በጎማ ወረዳ ቡሄኔ ወረዳ አቅራቢያ ቆሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን አልፎ ተርፎም ትላልቅ ህንፃዎችን አጥለቅልቋል። የመልሶ ግንባታ ጥረቶች ወራትን ሊወስዱ ይችላሉ።

"ቡሄኔ ሰፈር ያሉ ሁሉም ቤቶች ተቃጥለዋል" ሲሉ አንድ ነዋሪ ለአሶሺዬትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

እሳተ ገሞራው ጎማን ከቤኒ ከተማ ጋር የሚያገናኝ አንድ አውራ ጎዳና ተሻግሮ ቁልፍ የእርዳታ እና የአቅርቦት መንገድን ቆርጧል።

ቀደም ሲል የከተማዋን አውሮፕላን ማረፊያ ጎድቷል ቢባልም አየር ማረፊያው አለመጎዳቱ ታውቋል።

ከእሳተ ገሞራው ፍንዳታ በኋላ የመሬት መንቀጥቀጥ ተስተውሏል ሲሉ የመንግሥት ቃል አቀባይ ፓትሪክ ሙያያ ተናግረዋል። "ሰዎች አሁንም ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ በንቃት እንዲከታተሉ እና አላስፈላጊ ጉዞዎችን እንዳያደርጉ ብሎም የሚመከሩ አቅጣጫዎችን እንዲከተሉ እንጠይቃን" ብለዋል።

ከጎማ በ10 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኘው እሳተ ገሞራ ለመጨረሻ ጊዜ የፈነዳው እአአ በ2002 ሲሆን 250 ሰዎችን ገድሎ 120,000 ሰዎችን ቤት አልባ አድርጎ ነበር።

የጎማ ነዋሪዎች መንግሥት ከአካባቢው እንዲለቁ ከማወጁ በፊት ቤታቸውን ጥለው መሄድ መጀመራቸው ተዘግቧል። በምሽትም ፍራሾችን እና ሌሎች ንብረቶቻቸውን ይዘው በእግር ሲሸሹ ተስተውሏል።

የሩዋንዳ ባለሥልጣናት ከ3,000 በላይ ሰዎች ከጎማ ድንበር አቋርጠው መግባታቸውን ተናግረዋል። አንዳንዶቹ እሁድ መመለስ ሲጀምሩ ሌሎች ደግሞ ከከተማው ምዕራብ አቅጣጫ ከፍ ወዳለ ቦታ መሄዳቸውን ገልፀዋል።

ሪቻርድ ባህቲ የተባሉ የጎማ ነዋሪ ጩኸቱን ሲሰሙ ቤት ውስጥ እንደነበሩ እና ወደ ውጪ ሲመለከቱም ሰማይ ቀልቶ በማየታቸው እጅግ መጨነቃቸውን ተናግረዋል።

እአአ በ2002 ተከስቶ የነበረውን እሳተ ገሞራ የሚያስታውሱት ሪቻርድ፤ አሁን በእሳተ ጎሞራው "ቤቶቻችን እና ንብረቶቻችንን በሙሉ ወድመዋል" ሲሉም ገልፀዋል።

ቤታቸው የወደመባቸው ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters