ዲሞክራቲክ ሪፐብሊ ኮንጎ በረመዳን በዓል ግርግር ፈጥረዋል ባለቻቸው 29 ሰዎች ላይ የሞት ፍርድ ፈረደች

ታትሟል

ከሰሞኑ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊ ኮንጎ ዋና ከተማ ኪንሻሳ በኢድ በአል ላይ ከተነሳው ግጭት ጋር በተያያዘ 29 ሰዎች በሞት እንዲቀጡ ብይን መሰጠቱ ተሰምቷል።

በተቀናቃኝ የሙስሊም ቡድኖች መካከል በተነሳው ግጭት ምክንያት አንድ የፖሊስ አባል ህይወቱ ያለፈ ሲሆን በአስርታት የሚቆጠሩት ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በወቅቱ የቅዱሱ የረመዳን ወር መጠናቀቅን ለማክበር የእስልምና እምነት ተከታዯች በዋና ከተማዋ ተሰባስበው የነበረ ሲሆን የትኛው ቡድን ስነስርአቱን ይምራው በሚል በተፈጠረው አለመግባባት ነው የሰዎች ሕይወት እስከመጥፋት የደረሰው።

በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሕገ መንግስት መሰረት የሞት ቅጣት የማይፈጸም ሲሆን ፍርዱ የተላለፈባቸው ዜጎች ደግሞ የእድሜ ልክ እስር ይጠብቃቸዋል።

ሐሙስ ዕለት በተፈጠረው ይህ ግጭት ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተሳትፈዋል። ግርግሩን ተከትሎም ፖሊስ ሁኔታዎችን ለመቆጣጠር አስለቃሽ ጭስ ተጠቅሟል።

አንዳንድ የፖሊስ አባላት በተፈጠረው ግጭት ጉዳት ደርሶባቸው በአስጊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙና በሆስፒታል ህክምናቸውን እየተከታተሉ እንደሆነ የአገሪቱ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

በሐሙሱ ግጭት ላይ በሁለቱ የሙስሊም ማህበረሰቦች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት የማህበረሰብ መሪዎች አባብሰውታል ተብሏል።

እስካሁን 41 ግለሰቦች ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን አርብ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር።

በመላው አገሪቱ በቀጥታ ቴሌቪዥን የተላለፈው ይህ የፍርድ ሂደት በርካታ ሰአታት ፈጅቷል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች መካከል 31 ግለሰቦች ክስ ቀርቦባቸዋል። 29 ሰዎች ጥፋተኛ ተብለው የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ሲሆን ሁለት ሰዎች ደግሞ የአምስት ዓመት እስር ተፈርዶባቸዋል።