የሎተሪ አሸናፊዋ የ26 ሚሊዮን ዶላር ቲኬቷን በልብስ አጠባ እንዳጣችው አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, Smith Collection/Getty Images
የካሊፎርኒያ ነዋሪ የሆነች አንዲት ግለሰብ የ26 ሚሊዮን ዶላር አሸናፊ ያደረጋትን የሎተሪ ቲኬት ሱሪዋ ኪስ ውስጥ ረስታው በመታጠቡ ከጥቅም ውጭ መሆኑንን ለአሜሪካ ሚዲያዎች ተናግራለች።
ግለሰቡ ይህንን ያህል መጠን አሸናፊ ያደረጋትን ቲኬት የገዛችው ሎስ አንጀለስ በሚገኝ አንድ የገበያ መደብር ውስጥ ህዳር ወር ላይ ነበር።
ስሟ ያልተጠቀሰው ግለሰብ ቲኬቱን በወቅቱ ከመደብሩ ስትገዛ በካሜራ የተቀረፀች ሲሆን አሸናፊ የሚያደርጋት ቁጥር መያዟም ታውቋል።
የዕጣው አሸናፊ ገንዘብ የሚወስድበት የመጨረሻ ቀን በያዝነው ሳምንት ሃሙስ ነበር።
አሸናፊው እንደታወቀ ቲኬቱን በገዙበት በ180 ቀናት ሊወስዱ ይገባል።
ኤስፐራንዛ ሄርናንዴዝ የተባለው የገበያ መደብር ሰራተኛ የሆኑ ግለሰብ ካሊፎርኑያ ዊቲየር ደይሊ ኒውስ እንደተናገሩት በያዝነው ሳምንት ረቡዕ ሎተሪ ያሸነፈችው ግለሰብ መጥታ በአጋጣሚ ቲኬቷ ሱሪዋ ውስጥ ተረስቶ እንደታጠበ ተናግራለች።
የካሊፎርኒያ ሎተሪ ቃለ አቀባይ ካቲ ጆንሰን በበኩላቸው ለጋዜጣው እንደተናገሩት ግለሰቧ ቲኬቱን ስትገዛ የሚያሳየው የመደብሩ ቪዲዮ ገንዘቡን ለመጠየቅ በቂ እንዳልሆነና ቲኬቱን በእጇ መያዝ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ሆኖም ቪዲዮው ለሎተሪው አዘጋጅ አካል እንደደረሰና ቀጣይ ምርመራም እየተደረገበት እንደሆነ ካቲ ተናግረዋል።
የሎተሪው አሸናፊ ከሌለ ገንዘቡ ለካሊፎርኒያ የህዝብ ትምህርት ቤቶች እንደሚከፋፈል አዘጋጆቹ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
መግለጫው አክሎም አሸናፊ የሆነውን ቲኬት የሸጠው መደብር በአሰራሩ መሰረት 130 ሺህ ዶላር እንደተከፈላቸው መግለጫው አክሏል።
በካሊፎርኒያ ትልቅ ስፍራ ያለው ይህ ሎተሪ አሸናፊው ብሩን ሳይወስድ ሲቀር የተለመደ እንዳልሆነና አሸናፊም ነኝ ብሎ ቲኬት አለማሳየትም እንዲሁ የመጀመሪያ ነው ተብሏል።
በአውሮፖውያኑ 2016ም እንዲሁ አንዲት እንግሊዛዊት ሴት አሸናፊ የሆነችበትን የሎተሪ ቲኬት ቆሻሻ ጅንሷ ውስጥ ረስታው በልብስ ማጠቢያ ማሽን ውስጥ ገብቶ ከጥቅም ውጭ ሆኗል።












