ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አየር መንገዶች ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላንን እንዳያበሩ ዳግም ታገዱ
ከሁለት የመከስከስ አደጋ በኋላ ዳግም እንዲበር ፍቃድ አግኝቶ የነበረው የቦይንድ 737 ማክስ አውሮፕላን ዳግም አጣብቂኝ ውስጥ ገባ።
የኢትዮጵያ እና የኢንዶኔዢያው ላየን አየር መንገድ ንብረት የሆኑት የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች የመከስከስ አደጋ ካጋጠማቸው በኋላ በመላው ዓለም አውሮፕላኑ እንዳይበር እግድ ተጥሎበት እንደነበረ ይታወሳል።
ከስድስት ወራት በፊት ግን የአሜሪካ የበረራ ደህንነት ተቋማት አውሮፕላኑ ዳግም እንዲበር ፈቃድ ሰጥተው ነበር።
ይሁን እንጂ አውሮፕላኑ ሌላ የኤሌክትሪክ ችግር እንዳለበት በመታወቁ ዳግም ሌላ አጣበቂኝ ውስጥ መግባቱ ተነግሯል።
አውሮፕላኑ ዳግም ለማብረር የወሰኑ በመላው ዓለም የሚገኙ 24 አየር መንገዶች አውሮፕላኑን እንዳያበሩ ተነግሯቸዋል።
ይህም ብቻ ሳይሆን ቦይንግ ያመረታቸውን አውሮፕላኖች ከማከፋፈል ተቆጥቧል።
ቦይንግ እና የአሜሪካ የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር (ኤፍኤኤ) ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት እየሰራን ነው ብለዋል።
በአውሮፕላኑ ላይ የኤሌክትሪክ ችግር መገኘቱ ቀድሞውኑ አውሮፕላኑ ጥብቅ የደህንነት ፍተሻ ሳይካሄድበት ለበረራ ብቁ ነው መባሉ ሲተቹ ለነበሩ ሌላ የመከራከሪያ ነጥብ ሆኖላቸዋል።
ቦይንግን አጥቦቆ በመተቸት የሚታወቁት የቀድሞ የቦይንግ አስተዳዳሪ ኤድ ፒርሰን፤ በቦይንግ ፋብሪካ ያለው ደካማ የምርት ጥራት የኤሌክትሪክ ችግር እንደምክንያት በማንሳት የበርካቶችን ህይወት ለቀጠፉት አደጋዎች ምክንያቱ ይህ ሊሆን ይችላል ይላሉ።
ቦይንግ እና ኤፍኤኤ አውሮፕላኑ ላይ የተገኘው ችግር የኤሌክትሪክ ኃይል በሚያመነጨው ስርዓት ላይ ነው ብለዋል። ለዚህ መንስዔው የኤሌክትሪ ግነኙነቶች ሥራ ጥራት ደካማ መሆኑ ነው ይላሉ።
ኤፍኤኤ እንደሚለው የአሌክትሪክ ችግር፤ “መሠረታዊ የሆኑ የአውሮፕላኑ ስርዓት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል።”
ኤፍኤኤ ይህ የአውሮፕላኑ የኤሌክትሪክ ችግር ሳይቀረፍ አውሮፕላኑ አገልግሎት መስጠት የለበትም በማለት ከሁለት ሳምንት በፊት "አውሮፕላኑ ለመበረር የደህንነት ስጋት አለበት" የሚል መመሪያ አውጥቶ እንደነበረም ተጠቅሷል።
ቦይንግን 737 ማክስ አውሮፕላን የበረራ ቁጥር ኢቲ302 ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ናይሮቢ ሲበር ተከስክሶ ሁሉም ተሳፋሪዎች መሞታቸው ይታወሳል።
ተመሳሳይ የኢንዶኔዥያ ላየን ኤር ንብረት የሆነ አውሮፕላን ከኢንዶኔዢያ ተነስቶ ባህር ውስጥ መከስከሱ ይታወሳል።
በሁለቱ አደጋዎች በአጠቃላይ 346 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።