ኢትዮጵያ ከግዙፉ የወደብ አስተዳዳሪ ድርጅት ጋር ውል ገባች

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ከዲፒ ዎርልድ ጋር ሲፈራረሙ

የፎቶው ባለመብት, @dagmawit_moges

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

ኢትዮጵያ ከዓለማችን ግዙፍ የወደብ አንቀሳቃሾች መካከል አንዱ ከሆነው ዲፒ ዎርልድ ጋር የስምምነት ውል ገብታለች።

ስምምነቱ ኢትዮጵያን ከሶማሊንዱ በርበራ ወደብ ጋር ለማገናኘት የሚያስችል ነው ተብሏል።

የዩናይትድ አራብ ኤሜሬትስ ንብረት የሆነው ዲፒ ዎርልድ ፕሮጀክቱ "ቀጣናውን ለማበልፀግና ምጣኔ ሃብታዊ አቅምን ለማሳደግ ውይይት እንዲደረግ መንገድ ይከፋታል" ብሏል።

ፕሮጀክቱ ከራስ ገዟ የሶማሊላንድ በርበራ ወደብ ሁለቱን ሃገራት እስከሚያገናኘው የዋጃሌ ከተማ ድረስ ይዘረጋል።

የወደቡን ፕሮጀክት በትብብር የሚገነቡት የአቡ ዳቢ ዕድገት ፈንድና የዩናይትድ ኪንግደም ዓለም አቀፍ ዕድገት ናቸው።

ግንባታው በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ዲፒ ዎርልድ ከኢትዮጵያ ጋር በተገባው ውል [ሜሞራንደም ኦፍ አንደርስታንዲንግ] ውል መሠረት ዕቃ አስመጪና ላኪ ድርጅቶች በጥምረት እንዲሰሩ ያስችላል ይላል።

ድርጅቱ 1 ቢሊዮን ዶላር አፍስሶ ደረቅ ወደብ፣ ጎተራ፣ መጋዘን እንዲሁም ማቀዝቀዣ የተገጠመላቸው ማከማቸዎች ለመገንባት አቅዷል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ

"በርካታ ሥራዎች ይፈጥራል፤ አዳዲስ ቢዝነሶችና ኢንቨስተመንቶች ወደ ኮሪደሩ እንዲመጡ ያስችላል፤ አልፎም ሃገሪቱ ከዓለም አቀፍ ንግድ ጋር ያላትን ግንኙነት ያጠናክራል" ብለዋል የዲፒ ዎርልድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሱልጣን አሕመድ ቢን ሱሌይማን።

በርበራ ወደብ በቅርቡ ሰፊ የመልሶ ግንባታ እንደተሰራለት ይታወሳል።

በፈረንጆቹ 2016 ሶማሊላንድ ዲፒ ዎርልድን ቀጥራ ወደቧን ሰፋ አድርጎ እንዲገናባላት የ30 ዓመት ስምምነት መፈራረሙ አይዘነጋም።

በወቅቱ በየብስ የተከበበችው ኢትዮጵያ ከፕሮጀክቱ 19 በመቶ ድርሻ መጋራቷ ይታወሳል። 30 በመቶው ድርሻ የተያዘው በሶማሊላንድ ሲሆን የተቀረው 51 በመቶ ድርሻ የዲፒ ወርልድ ነው።

ዲፒ ዎርልድ በ442 ሚሊዮን ዶላር ወደቡን ለማስፋፋትና በዓመት 2 ሚሊዮን 20 ቻማ ርዝማኔ ያላቸውን ኮንቴነሮች ለመትከል ተስማምቷል።

ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከሁሉም ጎረቤት ሃገራት ጋር የንግድ መስመር ለመዘርጋት እንቅስቃሴ ጀምራለች።

ይህ እንቅስቃሴ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ላላት ኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት አጋዥ ነው እየተባለ ነው።

በስምምነቱ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ሃገራቸው "የወደብ መንገዶቿን የተሰባጠረ ለማድረግና ዕቃና አገልግሎት የሚመላለስበትን አማራጭ ለማስፋት እየሠራች ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከ95 በመቶ በላይ ዕቃዎችን የምታመላልሰው በጎረቤት ሃገር ጅቡቲ ወደብ በኩል ነው።

በፈረንጆቹ 2018 ኢትዮጵያ 750 ኪሎ ሜትር የሚዘረጋ በኤሌክትሪክ የሚሠራ ባቡር ወደ ጅቡቲ ወደብ መዘርጋቷ ይታወሳል።

የባቡር ግንባታው 4.5 ሚሊዮን ዶላር አውጥቷል።

አሁን የተገባው የበርበራ ወደብ ስምምነት በጅቡቲ በኩል ያለውን የዕቃዎች ምልልስ ወደ 50 በመቶ ዝቅ ሊያደርገው ይችላል ሲሉ ባለሙያዎች ይገምታሉ።