የጦር መሣሪያ፣ ቀስትና አደንዛዥ ዕፅ ይዞ ሲሲሊ የገባው ግለሰብ ተያዘ

የፖሊስ መኪና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ዜጋ በግል አውሮፕላን አደንዛዥ ዕፅና የጦር መሣሪያ ይዞ ከሃገር ሃገር በመብረሩ በቁጥጥር ሥር ውሏል።

ግለሰቡ ከአሜሪካዋ ፍሎሪዳ ግዛት ወደ ሲሲሊ አሊያ ሲቺሊያ ተብላ ወደ ምትጠራው የጣልያን ደሴት በሮ ሲያርፍ ነው በቁጥጥር ሥር የዋለው።

የ64 ዓመቱ ፓትሪክ ዮሴፍ ሆራን ወደ ጣልያኗ ደሴት የመጣሁት 'ዘመዶቼን ለመጎብኘት' ነው ሲል ለፖሊስ ተናግሯል።

አንሳ የተሰኘው የዜና ወኪል እንደዘገበው ሰውዬው ወደ ጣልያኗ ሲሲሊ የደረሰው ባለፈው አርብ ነው።

አውሮፕላኗ ስትፈተሽ ሰውዬው የጦር መሣሪያ፣ ቀስት እንዲሁም አንድ ኪሎ ግራም የሚመዝን ማሪዋና የተሰኘ ዕፅ ይዞ ነበር።

ፖሊስ መሣሪያዎቹንና ዕፁን 'ኤግዚቢት' ካደረገ በኋላ ሰውዬውን ወደ ከርቸሌ ወስዶታል።

የግል አውሮፕላኗ የሲሲሊ አውሮፕላን ማረፊያ ስትደርስ ነው በፖሊስ ተከባ ፍተሻ የተደረገባት።

በሲሲሊ የትራፓኒ ቢርጊ አውሮፕላን ማረፊያ የደረሱት ፖሊሶች ሁለት የእጅ ሽጉጦችና አንድ ትልቅ የጦር መሣሪያ እንዲሁም በካርቶን የታሸገ ቀለሃ አውሮፕላኗ ውስጥ አግኝተዋል።

አልፎም በላስቲክ የታሸገ አደንዛዥ ዕፅና የውሃ ኮዳዎች በቁጥጥር ሥር አውለዋል ሲል ላ ሪፐብሊካ ዘግቧል።

በግብርና ሥራ ተሰማርቶ ሃብት ያተረፈ ሰው ነው የተባለው ፓትሪክ በሲሲሊ ምዕራባዊ ግዛት የምትገኘው ሳንታ ኒንፋ ውስጥ አንድ የንግድ አጋር እንዳለው ተነግሯል።

ሰውዬው ለፖሊስ እንደተናገረው ወደ ሲሲሊ ዋና ከተማ ፓዬርሞ ሄዶ ሕክምና ሊያደርግ ነበር።

አሜሪካዊው ግለሰብ ፖሊስ ምርመራውን እስኪያጠናቅቅ ድረስ በፒዬትሮ ቼሩሊ ማረሚያ ቤት ይቆያል ተብሏል።

ከጣልያን 20 ክልሎች መካከል አንዷ የሆነችው ሲሲሊ ሜድትራኒያን ባሕር ላይ የምትገኝ ትልቋ ደሴት ናት።

አምስት ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ እንዳላት የሚነገርላት ጥንታዊቷ የሲሲሊ ከተማ የቱሪስ መዳረሻ ናት።