ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሶማሌ ክልል ኡለሞች 'ፈርኦናዊ የሴት ልጅ ግርዛትን' የሚከለክል ውሳኔ ለመስጠት ሊቀመጡ ነው
የሶማሌ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የሴት ልጅ የብልት ትልተላ እና መሰፋት ከእስልምና ሃይማኖት ጋር ቁርኝት እንደሌለው የሚገልፅ እና ተግባሩን የሚከለክል ብይን (ፈታዋ) ለመስጠት በቅርቡ እንደሚሰበሰብ ተገለፀ።
ምክር ቤቱ ያረቀቀው ይህ ፈታዋ የሴት ልጅን የብልት አካላት ከመቁረጥ ባሻገር ለሽንት ብቻ የሚሆን ቀዳዳ በመተው ሙሉ በሙሉ የመስፋት ሂደትን 'ፈርኦናዊ የሴት ልጅ ግርዛት' ሲል ጠርቶታል።
ይህም በዓለም የጤና ድርጅት መስፈርት መሰረት ሦስተኛ ደረጃ የሚባለው የብልት ትልተላ አይነት ሲሆን እጅግ የከፋ የሚባለውም ነው።
ኡለማዎቹ ከረመዳን ወር በኋላ በተቻለ ፍጥነት ተሰብስበው ረቂቁን ያፀድቁታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የክልሉ መጅሊስ ለቢቢሲ ገልጿል።
በሶማሌ ክልል ከሚገኙ 11 ዞኖች የሚመጡ ኡለሞች በጅግጂጋ ከተማ ተሰብሰበው ረቂቁን ካፀደቁት በኋላ ወደ ዐቃቤ ሕግ ተልኮ ሕግ ሆኖ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የዓለም የጤና ድርጅት ሦስተኛ ደረጃ የግርዛት ዓይነት የሚለው፣ የሴትን ልጅ ብልት የላይኛውን አካል በመቁረጥ እና ሁለቱን ከንፈሮች በመተልተል ብሎም ለሽንት የምትሆን ቀዳዳ ብቻ በማስቀረት ብልትን የመስፋት ተግባር ነው።
በተጨማሪም አንዲት የተሰፋች ሴት በምታገባበት ወቅት የተሰፋውን እንደገና በስለት የሚተረተር ይሆናል።
ረቂቅ ፈታዋው ምን ይላል?
ባለ 20 ገፁ ፈታዋ በቀዳሚ ገፆቹ ላይ የሰብአዊ መብቶችን ከቁርአን ጋር በማያያዝ ያብራራል። "በሸሪአ ማስረጃነት አንዲትን ነፍስ መግደል ወይም አካል መቁረጥም ሆነ መጉዳት የተከለከለ ነው" ሲል ያስረዳል።
የእስልምና ሐይማኖት አምስት የሰው ልጅ መብቶች ወይም ሐቆች እንዲረጋገጡ እንደሚያስቀምጥ እና ሸሪአም ይህንን የመፈፀም ዋና ግቡ መሆን እንዳለበት ይናገራል።
የእምነት፣ በህይወት የመኖር፣ የሃብት ባለቤትነት፣ የማንነት ክብር እና የአዕምሮ ነፃነቶች መሆናቸውን ገልፆ "እነዚህ መብቶች በክልላችን እንዲጓደሉ ያደረገውን ፈርኦናዊ የሴቶች ግርዛትን ለመከላከል እና በዚህ ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎች ላይ ብይን መስጠት ሸሪአዊ እና ሰብአዊ ግዴታ ነው" ሲል የብይኑን አስፈላጊነት ያስረዳል።
"ፈርኦናዊ የሴቶች ግርዛት በሴቶች ሰውነት ብሎም ህይወት ላይ ድንበር ያለፈ ጥቃት ነው፤ ለሴቶች በሐይማኖታቸው የተሰጣቸውን መብቶች የሚጎዳ አደገኛ ጎጂ ልማድ ነው" ሲልም ድርጊቱን ያወግዛል።
ረቂቅ ፈታዋው ከሰብአዊ መብቶች ባሻገርም ተግባሩ የሚያመጣውን የጤና ጉዳት በሳይንሳዊ ጥናቶች እና በእስላማዊ ምሁራን የተሰሩ ዳሰሳዎችን በማጣቀስ ዘርዝሯል። ድርጊቱ በሥነ ልቦና ላይ የሚያመጣቸውንም ጉዳቶች አትቷል።
የፈታዋ ኮሚቴው 14 ምክረ ሃሳቦችን ያስቀመጠ ሲሆን በተለይም በመጀመሪያ ሁለት ነጥቦቹ ላይ በሴቶች ግርዛት ላይ ቁርጠኛ አቋም ይዟል።
"የሴቶች ግርዛት ሴትን ልጅ የሚጎዳ ተግባር ስለሆነ እንከላከላለን እናወግዛለን" የሚለው የመጀመሪያ ነጥቡ ሲሆን ቀጥሎም "ፈርኦናዊውን ግርዛት ለመከላከል ከሕግ አካላት ጋር በጋራ መስራት" ሲልም አስቀምጧል።
በሶማሌ ክልል መጅሊስ ውስጥ የፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት አብዲ አብዱላሂ፣ ይህ ፈታዋ ሐይማኖታዊ ትርጉም እየተሰጠው ክልሉ ያሉ ሴት ልጆች ላይ ሲደርስ የቆየውን ተግባር ለማስቆም ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል ሲሉ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
በተለይም ከዐቃቤ ሕግ፣ ከፖሊስ አና ከፍርድ ቤት ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችል ስለሚሆን በኡለማዎች ከፀደቀ በኋላ ወደ ሕግነት መቀየሩ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋልም ብለዋል።
በሌሎች የምክረ ሃሳቡ ክፍሎች ላይም በተለይም በተለያዩ አማራጮች ኅብረሰተሰቡን ማስተማር እና የሚመለከታቸውን ባለድርሻዎች ማሳተፍ ቁልፍ ተብለው ተዘርዝረዋል።
እንዲሁም በመግረዝ ተግባር የሚተዳደሩ ሰዎችን አማራጭ የሥራ እድል መፍጠር እና ከዚህ ድርጊት እንዲወጡ ማስቻል ሌላው ቁልፍ ተብሎ የተነሳ ሃሳብ ነው።
የብይኑ መጽደቅ ምን ልዩነት ያመጣል?
የፕሮግራም አስተባባሪው አብዲ አብዱላሂ እንደሚሉት ይህ ፈታዋ መጽደቅ በሶማሌ ክልል ድርጊቱ ሐይማኖታዊ ነው ብሎ በማሰብ የሚፈፀም በመሆኑ ምክንያት ይህ ውሳኔ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ይህ ፈርኦናዊ የሚባለው ግርዛት በሶማሌ ክልል ከ90 በመቶ በላይ የሚተገበር የግርዛት አይነት መሆኑን የሚገልፁት አብዲ፣ ለዚህ ነው በዚህ ላይ ቅድሚያ የሰጠነው ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በመላው ሶማሌ ክልል ያሉ ኡለሞች ተሰብስበው ይህንን ረቂቅ ፈታዋ ካፀደቁት የሴትን ልጅ ብልት መተልተል እና መስፋት ሃራም [የተከለከለ] ተብሎ የሚወገዝ ይሆናል።
ረቂቅ ፈተዋው "ፈርኦናዊው የሴቶች ግርዛት በቅዱስ ቁርአን፣ በነብዩ ሃዲስ (ሱና)፣ በኡለማዎች እጅመዕ መሰረት ሃራም መሆኑ ተረጋግጧል" የሚል ፍርድ ኡለማዎቹ እንዲወስኑበት የቀረበው ብይን ነው።
በተጨማሪም ይህንን ተግባር የፈፀመ ሰው ቅጣቱ ሙሉ የደም ካሳ እንደሆነ ይገልፃል።