ኮሮናቫይረስ፡ ሜክሲኮ በኮቪድ-19 የሞቱብኝ ዜጎች ቁጥርን አምታትቻለሁ አለች

በሜክሲኮ ቀደም ሲል በቫይረሱ ሞተዋል ተብሎ የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር በ60 በመቶ ጨምሯል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በሜክሲኮ ቀደም ሲል በቫይረሱ ሞተዋል ተብሎ የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር በ60 በመቶ ጨምሯል
ታትሟል

ሜክሲኮ በኮቪድ-19 ተህዋሲ የሞቱባትን ዜጎች ቁጥር ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ አዲስ መረጃን ይፋ አድርጋለች። አዲሱ መረጃ ከዚህ ቀደም በአገሪቱ ውስጥ ሞተዋል ተብሎ ከተገለጸው አሃዝ በ60 ከመቶ የጨመረ ሆኗል።

አሁን ባለው መረጃ ሜክሲኮ ከ321,000 በላይ ዜጎቿ ይህ ተህዋሲ ባመጣው ጣጣ ሕይወታቸውን ማጣታቸው ተረጋግጧል።

ይህ አዲሱ አሃዝ ሜክሲኮ በዓለም ብዙ ሰዎችን በተህዋሲው ምክንያት በማጣት አሜሪካንን ተከትላ 2ኛዋ አገር ያደርጋታል።

ፕሬዝዳንት አንድሩ ማኑዋል ሎፔዝ አብራዶር ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሄዱበት መንገድ ብዙዎች ሲተቹት ነበር።

በተለይ ተቃዋሚዎች ፕሬዝዳንቱን የተህዋሲውን ገዳይነት አሳንሰው አይተዋል፣ ክትባት የሚሰጥበትን ፍጥነት አዘግይተዋል በሚል ይከሷቸዋል።

በሜክሲኮ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይፋ የተደረገው አዲሱ አሃዝ በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት 6ኛው ሳምንት መጨረሻ ላይ በአገሪቱ በተህዋሲው የሞቱት ሰዎች 294,287 እንደነበር ይመሰክራል።

ይህም ከዚህ ቀደም 182,301 ብቻ ሟቾች እንደሆኑ የተገለጸበትን ሪፖርት ውድቅ የሚያደርግ ነው።

ከየካቲት አጋማሽ ጀምሮ ብቻ እስከ አሁን ባለው ወቅት 26 ሺህ ሰዎች በሜክሲኮ በኮቪድ-19 የተነሳ ሞተዋል።

ይህ ቁጥር ሜክሲኮን ከብራዚል በልጣ እንድትገኝ ያደርጋታል።

ብራዚል በተህዋሲው 310 ሺህ ሰዎች እንደሞቱባት ነው ያስመዘገበችው።

በዓለም በሟቾች ቁጥር ቀዳሚ ሆና ያለችው አሜሪካ ስትሆን እስከዛሬ 549 ሺህ ዜጎቿን አጥታለች።

በሜክሲኮ የጤና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ የሟቾች ቁጥር በይፋ ከተገለጸው በብዙ እጥፍ በላይ ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ሲሰጡ ነበር።

የቁጥሩ መዛባት የመጣው የሚመመረመሩ ሰዎች ማነስና በርካታ ዜጎችም ሆስፒታል ሳይገቡ በቤታቸው ሆነው መሞታቸው ነው ተብሏል።

አዲሱ አሃዝ የሟቾችን የሞት ሰርተፍኬት በማተም ሂደት የተገኘ መሆኑም ተመላክቷል።

በሜክሲኮ ለፋሲካ በርካታ ሰዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ሊንቀሳቀሱ ስለሚችሉ ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ ሊዛመት እንደሚችል ስጋት አለ።

ሜክሲኮ ለዜጎቿ ክትባቱን ማደል የቀጠለች ሲሆን እስከዛሬ ከ6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተከትበዋል።

አሜሪካ በቅርቡ 4 ሚሊዮን የአስትራዜኒካ የክትባት ብልቃጦችን ለሜክሲኮና ለካናዳ እስደምትሰጥ ይፋ አድርጋለች።

ሁለቱ ተቀባይ አገራት አስትራዜኒካ ጥቅም ላይ እንዲውል ያጸደቁ ሲሆን አሜሪካ ግን ክትባቱን ሳታጸድቅ ለማንኛውም በሚል ይዛው ቆይታለች።