ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ብሪትኒ ስፒርስ 'አባቴ እኔን ከመቆጣጠር ይታገድልኝ' ስትል ለፍርድ ቤት አመለከተች
የታዋቂዋ አሜሪካዊት ሙዚቀኛ ብሪትኒ ስፒርስ ጠበቃዎች አባቷ ከተቆጣጣሪነት እንዲታገድ በይፋ ለፍርድ ቤት ዳኛ አመልክተዋል።
የፖፕ ሙዚቃ ኮከብ የሆነች ብሪትኒ በፈረንጆቹ ከ2008 ጀምሮ አባቷ ግላዊ ጉዳዮቿን እንዲቆጣጠር በፍርድ ቤት አስወስና ነበር።
አባቷ ጄሚ ስፒርስ በጤና እክል ምክንያት ከዚህ ሥልጣናቸው ከወረዱ በኋላ ጆዲ ሞንትጎመሪ የተሰኙ ሰው በምትካቸው ተቀጥረዋል።
ብሪትኒ አሁን አባቴ ቀርቶብኝ ሞንትጎመሪ የተሰኙት ሰው ቋሚ ይሁኑልኝ እያለች ነው።
የግል ጉዳዪች ጠባቂ ምን ማለት ነው?
የግል ጉዳዮች ጠባቂ ወይ ተወካይ ማለት በፍርድ ቤት በሚደረስ ስምምነት የአንድን ሰው ንብረት፣ ግላዊ ግንኙነቶች እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን የሚቆጣጠር ማለት ነው።
የብሪትኒና የአባቷ ውል በሁለት የሚከፈል ነው። አንደኛው የአባቷ ሥራ የግምዣ ቤት ኃላፊነት ነው።
በሁለተኛ ደረጃ አባቷ ሃብትና ንብረቷን ከመቆጣጠር አልፈው እሷን የመቆጣጠር መብት ተሰጥቷቸዋል።
የሙዚቀኛዋ አባት በፈረንጆቹ 2019 በጤና እክል ምክንያት የለቀቁት ሥልጣን እሷን የመቆጣጠር እንጂ የሃብትና ንብረቱን አይደለም።
ጆዲ ሞንቶጎመሪ የተሰኙት ግለሰብ በሙያው የበቁ ሰው ናቸው። የብሪትኒ አባት ሲወርዱ ነው በምትካቸው የተሾሙት።
ነገር ግን ሹመታቸው አልፀናም። የብሪትኒ ጠበቆች አሁን ሰውዬው ቋሚ እንዲሆኑ ነው ለፍርድ ቤት ዳኛ ጥያቄ ያቀረቡት።
የ39 ዓመቷ አቀንቃኝ ጠበቃ ሳሙዔል ዲ ኢንግሃም ሎስ አንጀለስ ለሚገኙ አንድ ዳኛ ይህን ጥያቄ በይፋ አቅርበዋል።
በተጨማሪም ብሪትኒ ስፒርስ አባቷ ግላዊ ጉዳዮቿን ከመቆጣጠር እንዲነሳላትም ለፍርድ ቤት ጥያቄ ማቅረቧን የችሎት ወሬዎች ሹክ ብለዋል።
ብሪትኒ ውሉን ስትፈፅም ያስገባችው የፍርድ ቤት ሰነድ እንደሚያሳየው አባቷ ከበላይ ጠበቂነት እንዲነሱ መጠየቅ ትችላለች።
ከዚህ በፊት የብሪትኒ ጠበቆች ደንበኛችን [ብሪትኒ] አባቷን ትፈራዋለች፤ አባቷ የግል ጉዳዮቿ ተቆጣጣሪ እስከሆኑ ድረስ ለሙዚቃ ሥራ ወደ መድረክ አትመለስም ብለው ነበር።
የአባቷ ጠበቃ ደግሞ በበኩላቸው ደንበኛዬ "ቀና፣ ሰው ወዳድና ታማኝ አባት ናቸው" አልፎም ብሪትኒ እንዳትበዘበዝ አድርገዋል ይላሉ።
አዲሷ የብሪትኒ የግል ጉዳዮች ጠባቂ ከጠበቃዋ ውጭ ብሪትኒን ለመገብኘት የሚመጡ ሰዎች ማገድ ይችላሉ።
አልፎም ከጤና ባለሙያ ጋር ስለጤናዋ ማውራትና የሕክምና ሰነዷን ማየት ይችላሉ።
ጠባቂዋ ከዚህም በዘለለ ለዘፋኟ ጠባቂዎችና ተንከባካቢዎች መመደብና እንዲሁም ማባረር ይችላሉ፤ ዘፋኟ ላይ አንድ ጉዳት ከደረሰም የመክሰስ መብት አላቸው።
የብሪትኒ አባት ከግላዊ ጉዳዮቿ ተቆጣጣሪነት ይነሱ እንጂ አሁንም የ60 ሚሊዮን ዶላር ሃብቷ ጠባቂ ናቸው።
አሁን ባለው የፍርድ ቤት ስምምነት መሠረት ብሪትኒ ስፒርስ ከ2008 ጀምሮ ሃብትና ንበረቷን ተቆጣጥራም ቆጥራም አታውቅም።
ፍርድ ቤት ቀጣይ ቀጠሮ ለሚቀጥለው ወር ሰጥቷል።
ብሪትኒ ስፒርስ ከሰሞኑ የመገናኝ ብዙሃን ትኩረት የሆነችው ብዙ ከተባለለትና የግሉ ታሪኩን ከሚተርከው ዘጋቢ ፊልም በኋላ ነው።