በሕመም ምክንያት ማንበብና መጻፍ ሳይችል የቆየው ሶስተኛ ዲግሪውን እየሰራ ነው

ታትሟል

እስከ 13 ዓመት እድሜው ድረስ ማንበብና መጻፍ ሳይችል የቆው ዊሊያም ካርተር በፖለቲካል ሳይንስ ሦስተኛ ዲግሪውን [የዶክትሬት] ለማግኘት እየሰራ ነው።

የ22 ዓመት ወጣቱ ዊሊያም ካርተር የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ እያለ ማንበብ ባለመቻሉ ይሳቅበት እንደነበር ተገልጿል።

ለዚህም ምክንያቱ ዊሊያም ዲስሌክሲያ እና ዲስፕራክሲያ የተሰኙ ሕመሞች ነበሩ።

ዲስሌክሲያ እንዳለበት ከታወቀ በኋላ ግን በፍጥነት ውጤቱ መሻሻል መጀመሩን ተገልጿል።

ዲስሌክሲያ በሌላ ስሙ የማንበብ ቀርነት የሚያስከትል ሕመም በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ ታዳጊዎች የንግግር ድምፆችን መለየት ባለመቻል የተነሳ ማንበብ እንዳይችሉ ያደርጋል።

በዲስሌክሲያ የተጠቁ ታዳጊዎች በልዩ ፍላጎት ትምህርት ከታገዙ ውጤታማ እንደሚሆኑ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።

ዲስፕሬክሲያ በበኩሉ የእድገት ጥምረት ጉዳት ሲሆን አካልን በሚገባ ለማዘዝ የመቸገር ሕመም መሆኑ ይነገራል።

ካርተር በፖለቲካ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት የመጀመሪያ ዲግሪውን ከብሪስቶል ዩኒቨርስቲ ያገኘ ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ በሚገኝ ዩኒቨርስቲ እየተማረ ነው።

"ማንበብና መጻፍ መማሬ ዓለምን የበለጠ እንድረዳ እንዲሁም ደግሞ ለዓለም የበለጠ እንድቀርብ አድርጎኛል" ብሏል።

"በመሰረታዊነት ዲስሌክሲያ አሁን የሆንኩትን እንድሆን አግዞኛል" ሲልም አክሏል።

የምዕራብ ለንደን ነዋሪ የሆነው ካርተር በምርጥ ተማሪነቱ ሽልማት ተቀብሏል።

በፓለቲካ ቲዮሪ (ኀልዮት) እና ብላክ ጂኦግራፊ ፕሮፌሰር ለመሆን ያለመ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላም "ላይጠገን የተበላሸውን ሥርዓት" ለመለወጥ በፖለቲካ መሳተፍ እንደሚፈልግ አሳውቋል።

ካርተር በአሁኑ ወቅት በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ፣ በርክሌይ የፖለቲካል ጂኦግራፊ የሦስተኛ ዲግሪውን እያጠና ይገኛል።