ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጂቡቲ ወደ ባህር የተወረወሩ ቢያንስ 20 የሚሆኑ ስደተኞች ሕይወት አለፈ- የተባበሩት መንግሥታት
ቢያንስ 20 የሚሆኑ አፍሪካውያን ስደተኞች በጅቡቲ ባህር ዳርቻ አካባቢ በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከጀልባ ላይ ተወርውረው ሕይወታቸው ማለፉን የተባበሩት መንግስታት አስታወቀ።
የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) በበኩሉ አዘዋዋሪዎቹ ጀልባው ከሚገባው በላይ መሙላቱን ሲያስተውሉ "ቢያንስ 80 የሚሆኑትን ስደተኞች ወደ ውሃ ገፍትረዋቸዋል" ብሏል።
ጀልባው 200 የሚሆኑ ስደተኞችን ጭኖ የነበረ ሲሆን ከስደተኞቹ መካከልም ሴቶችና ህጻናት ይገኙ እንደነበር የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት አስታውቋል።
አብዛኛዎቹ ስደተኞች ወደ የመን ጉዟቸውን እያደረጉ የነበረ ሲሆን ከየመን ደግሞ ወደ ሳኡዲ አረቢያ በማቅናት የተሻለ ህይወትና ስራ ለማግኝት የሚሞክሩ ናቸው።
የስደተኞቹን ሞት በተመለከ መረጃውን ይፋ ያደረጉት የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ኃላፊው አንቶኒዮ ቪቶርኖ ናቸው።
በማህበራዊ ሚዲያው ትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ' ዛሬ በጅቡቲ የውሃ ድንበር አካባቢ መጥፎ ዜና ተሰምቷል። በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከጀልባ ላይ ከተገፈተሩ በኋላ ቢያንስ 20 የሚሆኑ ስደተኞች ሰጥመው ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን ሌሎች 60 የሚሆኑትና ወደ ውሃ የተገፈተሩት ደግሞ ችግር ላይ ናቸው'' ብለዋል።
አክለውም "ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ኢላማ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች አዘዋዋሪዎችን በሕግ መጠየቅ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል'' ብለዋል።
በተለይ ከሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የሚነሱ ስደተኞች በጅቡቲ የባህር ክልል አካባቢ በተደጋጋሚ አደጋ የሚያጋጥማቸው ሲሆን በርካቶችም ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ከነዚህ አገራት የሚነሱ በርካታ ስደተኞችም ለተሻለ ህይወት ወደ ገልፍ አገራት የሚያቀኑ ናቸው።