በአፍጋኒስታን ሦስት የመገናኛ ብዙሃን ሰራተኞች በጥይት ተመትተው ተገደሉ

አፍጋኒስታን

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

በአፍጋኒስታኗ ጃላላባድ ከተማ ሦስት የቴሌቪዥን ጣቢያ ሰራተኞች በጥይት ተመትተው ተገደሉ።

እድሜያቸው ከ18-20 መካከል የሚገኙት ሴቶች የተገደሉት በተለያየ ስፍራ በተቀናጀ ሁኔታ ነው።

ሌላ አራተኛ የተመሳሳይ መገናኛ ብዙሃን ሰራተኛ በጥይት ተመትታ ለሕይወት አስጊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በሆስፒታል እንደምትገኝ ተነግሯል።

ፖሊስ ከታሊባን ጋር ግነኙነት አለው ያለውን አንድ ታጣቂ በቁጥጥር ሥር አውሏል። ታሊባን ግን በግድያው ተሳትፎ የለኝም ብሏል።

በአፍጋኒስታን በተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች ኢላማ ተደርገው ጥቃት ይፈጸምባቸዋል።

ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት አራቱ ወጣት ሴቶች በቅርቡ ትምህርታቸውን አጠናቀው ኢኒካስ የተባለ ቴሌቪዥን ጣቢያ መስራት በጀመሩ ጥቂት ወራት ውስጥ ነው ጥቃቱ የተፈጸመባቸው።

“ሁሉም ተገድለዋል። ከሥራ ቦታቸው ወደ መኖሪያ ቤታቸው በእግራቸው እየተጓዙ ሳለ ነው የተገደሉት” ሲሉ የቴሌቪዥን ጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ኤኤፍፒ ጨምሮ እንደዘገበው ፖሊስ በጥቃቱ ተሳታፊ ናቸው ያላቸውን ሰዎች በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየሰራ ነው። የአካባቢው የፖሊስ አዛዥ በቁጥጥር ሥር የዋላው ታጣቂ፤ ጥቃቱን መፈጸሙን እና የታሊባን አባል መሆኑን አምኗል ሲሉ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።

በአፍጋኒስታን ተሰማርቶ የነበረው የአሜሪካ ጦር ከታሊባን ጋር የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ ከአገሪቱ በመውጣቱ በአፍጋኒስታን መሰል ተደጋጋሚ ጥቃቶች እየደረሱ ይገኛሉ።

ከሁለት ወራት በፊት በተመሳሳይ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ የነበረች ሴት በጥይት ተመትታ ተገድላ ነበረ። አይኤስ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን ወስዷል።

ከአንድ ወር በፊት ደገሞ በአፍጋኒስታን መዲና ካቡል ሁለት ሴት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች በጥይት ተመትተው ተገድለው ነበር።