ኮሮናቫይረስ፡ የአሜሪካ ታችኛው ምክር ቤት ጆ ባይደን ያቀረቡትን የ1.9 ትሪሊየን ዶላር ድጎማ አፀደቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት አሜሪካዊያንን ለመርዳት ያቀረቡት የ1.9 ትሪሊየን ዶላር የኢኮኖሚ ማነቃቂያ ማዕቀፍ በተወካዮች ምክር ቤት ፀደቀ።
የድምፅ አሰጣጥ ሁኔታው ከፓርቲ ወገንተኝነት ጋር የተያያዘ ነበር። ሁሉም ሪፐብሊካኖች ተቃውመውታል።
ሁለት ዲሞክራቶችም ገንዘቡ በጣም ብዙ ነው ሲሉ በመቃወም ሪፐብሊካኖችን ተቀላቅለዋል።
ማዕቀፉ በሚቀጥለው ሳምንት የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ዲሞክራቷ ካማላ ሃሪስ ሰብሳቢ በሆኑበት የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ይቀርባል።
ይህ ምክር ቤት ከየግዛቱ እኩል 2 እንደራሴዎች የሚሞሉት የመቶ ወኪሎች ሸንጎ ነው። ባለ ትልቅ ሥልጣንም ነው።
ምክር ቤቱ ዝቅተኛ የክፍያ መጠንን በእጥፍ ማሳደግ የሚለውን ሃሳብ ውድቅ አድርጓል።
ይህ ረቂቅ ሕግ ግን አሁንም የአሜሪካ ዝቅተኛ ክፍያ ጭማሬን አካቷል።
ይህ እንዴት እንደሚፈታ ግልፅ የሆነ ነገር የለም።
ምንም እንኳን በምክር ቤቱ ይህ ነጥብ እንዳይካተት ቢደረግም የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ፤ ሁሉም የቀረቡት እቅዶች እንደሚያልፉ ተናግረዋል።
ዝቅተኛ ክፍያን ማሳደግ የዲሞክራቶች ዋነኛ ግብ ነው። አንዳንድ የዲሞክራት መሪዎች በሰዓት ከ15 ዶላር በታች የሚከፍሉ ቀጣሪዎችን ለመቅጣት እያሰቡ ነው።
ይህ የገንዘብ ማዕቀፍ የኮሮናቫይረስ ክትባት ስርጭትን እና ምርመራን ለማሳደግ እንዲሁም ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት ያለመ ነው።
ማዕቀፉ ለሁሉም አሜሪካዊያን ከሚሰጠው 1 ሺህ 400 ዶላር የገንዘብ ድጎማ ጋር ተደማምሮ ለቤተሰብ የሚሰጠውን ድጎማ 1 ትሪሊየን ዶላር ገንዘብን ያካትታል።
ከዚህም ባሻገር ወረርሽኙን ለመዋጋት የሚውል 70 ቢሊዮን ዶላር እና ለአነስተኛ ንግዶች ማነቃቂያ 110 ቢሊየን ዶላርንም ይጨምራል ።
ለቤተሰብ፣ ለአነስተኛ የንግድ ተቋማትንና የግዛት መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ይሆናልም ተብሏል።
ዲሞክራቶች ቅዳሜ ጠዋት በተደረገው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት በቂ ድምፅ አግኝተዋል።
በዚህም ፕሬዚደንት ባይደን በኮቪድ -19 እየተፈተኑ ያሉትን አሜሪካዊያን ለመርዳት ባሰቡት 'የአሜሪካ መታዳጊያ እቅድ' አሸናፊ ሆነዋል።
ይሁን እንጂ ሪፐብሊካን እቅዱ አላስፈላጊ በሆነ መጠን ብዙ እና ከወረርሽኙ ጋር ተያያዥነት በሌላቸው ዲሞክራሲያዊ ጉዳዮች የተሞላ ነው ብለዋል።
ዲሞክራቶች በላዕላይ ምክር ቤቱ ጥብቅ ክርክር ይጠብቃቸዋል ተብሏል።
ዲሞክራቱ ጆ ባይደን በአሜሪካ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የገደለውን ወረርሽኝ ለመዋጋት ቃል መግባታቸው ይታወሳል።












