የኤል ቻፖ ሚስት 'በዕጽ ዝውውር' አሜሪካ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋለች

ኤማ ኮሮኔል አስፑሮ የኤል ቻፖ ባለቤት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ኤማ ኮሮኔል አስፑሮ የኤል ቻፖ ባለቤት
ታትሟል

የሜክሲኳዊው ዕጽ አዘዋዋሪ ጆአኪን "ኤል ቻፖ" ጉዝማን ሚስት በእጽ ዝውውር ተጠርጥራ አሜሪካ ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋሏን የአሜሪካ ባለስልጣናት ገለጹ።

የ31 ዓመቷ ኤማ ኮርኔል አይስፑሮ ዋሽንግተን ዲሲ አቅራቢያ በሚገኘው ደለስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ነው በቁጥጥር ስር የዋለችው።

ኮኬይን፣ ሜታአምፌታሚን፣ ሄሮይን እና ማሪዋና የተባሉ ዕጾችን በማሰራጨት ተግባር ተሠማርታለች በሚል ክስ ቀርቦባታል።

ኤል ቻፖ በዕጽ ዝውውር እና በሐሰተኛ ገንዘብ ዝውውር ዕድሜ ልክ ተፈርዶበት በኒው ዮርክ እስር ቤት ውስጥ ይገኛል።

የ63 ዓመቱ ሜክሲኳዊ 'ሲናሎዋ' የሚባለው ቡድን የበላይ ሲሆን ባለስልጣናት እንደሚሉት ቡድኑ በአሜሪካ የዕጽ ዝውውር ቀዳሚውን ደረጃ ይይዛል።

የኤል ቻፖ ጉዳይ በጎርጎሮሳዊያኑ 2019 በታየበት የፍርድ ሂደት የ13 ዓመት ልጆችን በዕጽ በማደንዘዝ ከመድፈር ጀምሮ የተቀናቃኝ እና የራሱን ቡድን አባላትን እስከመግደል የሚደርስ ወንጀል መፈጸሙ ተገልጿል።

አሁን በቁጥጥር ስር የዋለችው ባለቤቱ ዲሲ ውስጥ በሚገኘው የፌደራል ፍርድ ቤት በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካይነት እንደምትቅርብ አሜሪካ ፍትህ መስሪያ ቤት አስታውቋል።

ከዕጽ ዝውውር በተጨማሪ በጎርጎሮሳዊያኑ 2015 ባሏ ከሜክሲኮ ማረሚያ ቤት እንዲያመልጥ ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን አግዛዋለች የሚል ክስም ቀርቦባታል።

ኤል ቻፖ ለልጆቹ ታስሮበት ከነበረው በማረሚያ ቤት አቅራቢያ ንብረት ከገዛ እና በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ማረሚያ ቤቱ የገባ የአቅጣጫ መጠቆሚያ (ጂፒኤስ) ያለው ሰዓት በመጠቀም በሜክሲኮ ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግለት ከአልቲፕላኖ እስር ቤት ለማምለት ችሎ ነበር።

ከመሬት በታች በተቆፈረ መተላለፊያ ከእስር ቤቱ ካመለጠ በኋላም ከዋሻው ውስጥ በልዩ ሁኔታ በተሠራች አነስተኛ ሞተር ብስክሌት አማካይነት ለመውታት ችሏል።

የፍርድ ቤት ሰነዶች እንደሚያሳዩት ኤል ቻፖ በጎርጎሮሳዊያኑ ጥር 2017 ለአሜሪካ ተላልፎ ከመሰጠቱ በፊት ባሏን ከእስር እንዲያመልጥ በማቀድ ኮርኔል አይስፑሮ ተሳትፋለች ተብሏል።

እሷ ግን በተከሰሰችበት ጉዳይ ላይ የሰጠችው አስተያየት የለም።

ኮርኔል አይስፑሮ የአሜሪካና ሜክሲኮ ጥምር ዜግነት ሲኖራት የኤል ቻፖ ጉዝማን መንትያ ልጆችም እናት ናት።

ባለቤቷ በኒው ዮርክ የነበረውን የሦስት ወር የፍርድ ሂደት በየቀኑ በሚባል ሁኔታ የተካፈለች ሲሆን አስከፊ ከሆኑት የግድያ እና የአስገድዶ መድፈር ክሶቹ ብቻ ሳይሆን በእርሷና በሌሎች ሴቶች ላይ ክትትል ያስደርግ እንደነበር ሰምታለች።

ባለቤቱ ችሎቱ ባሏ ላይ ከወሰነና ሂደቱ ካበቃ በኋላ ታማኝነቷን ጠብቃ ቆይታለች። "ባለቤቴን እሱን ለማሳየት እንደሚሞክሩት ሆኖ አላውቅም። ይልቁንም የማደንቀው እንዳገኘሁት እና እንዳገባሁት ሰው ነው" ብላለች።

ጉዝማን በሰሜን ምዕራብ ሜክሲኮ ከምትገኘው ሲናሎዋ ግዛት ከአንድ ድሃ ቤተሰብ የመጣ ሲሆን ያደራጀው የወንጀል ቡድን በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ በፎርብስ የ2009 የዓለማችን ሀብታም ሰዎች ዝርዝር አንድ ቢሊዮን ዶላር በሚገመት ሀብቱ 701ኛ ደረጃን ይዞ ነበር።

ጆአኪን "ኤል ቻፖ" ጉዝማን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ጆአኪን "ኤል ቻፖ" ጉዝማን በፖሊስ ተይዞ