በኒው ዚላንድ ትምህርት ቤቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ በነጻ ሊሰጥ ነው

ታትሟል

በኒው ዚላንድ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ባጠቃላይ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ በነጻ ሊያቀርቡ ነው።

ከቀጣዩ ሰኔ አንስቶ ትምህርት ቤቶቹ የንጽህና መጠበቂያ እንደሚሰጡ ተገልጿል።

ሴቶች የወር አበባቸው ሲመጣ የንጽህና መጠበቂያ ለመግዛት አቅም ሲያጡ ትምህርት ቤት ይቀራሉ።

የአገሪቱ አመራሮች በወር አበባ ምክንያት ማንኛዋም ሴት ከትምህርት ቤት እንዳትቀር በሚል ይህን ውሳኔ እንዳስተላለፉ ተገልጿል።

አምና በ15 ትምህርት ቤቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ በነጻ ለመስጠት ሙከራ ተደርጎ ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትር ጀሲንዳ አርደን "ታዳጊ ሴቶች ተፈጥሯዊ በሆነው የወር አበባ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው መቅረት የለባቸውም" ብለዋል።

ኒው ዚላንድ ውስጥ ከ12 ሴቶች አንዷ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ በማጣት ከትምህርት ቤት እንደምትቀርም ጠቅላይ ሚንስትሯ ተናግረዋል።

ዝቅተኛ ገቢ ካለው ቤተሰብ የተገኙና አቅመ ደካማ ታዳጊዎች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ለመግዛት ስለማይችሉ በየወሩ ከትምህርት ገበታቸው ይሰናከላሉ።

የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ መስጠት መንግሥት ድህነትን ከሚዋጋባቸው መንገዶች አንዱ እንደሆ ጠቅላይ ሚንስትሯ አስረድተዋል።

መንግሥት በዚህ መንገድ ታዳጊዎች ከትምህርት እንዳይስተጓጎሉና ጤናቸው እንዲጠበቅም እንደሚያደርግ አያይዘው ጠቅሰዋል።

በትምህርት ቤቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ በነጻ ለመስጠት ኒው ዚላንድ እስከ አውሮፓውያኑ 2024 ድረስ 25 ሚሊዮን ዶላር ታወጣለች።

ባለፈው ጥቅምት ስኮትላንድ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ በነጻ በማደል የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች።

እንግሊዝ ውስጥ ለመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ በነጻ ይሰጣል። በርካታ የአሜሪካ ግዛቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ በነጻ እንዲሰጥ የሚያዘውን ሕግ አጽድቀዋል።

በኢትዮጵያም በመሰረታዊ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ላይ የቀረጥና የታክስ ማሻሻያ መደረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል። ይህም የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ገበያ ላይ የሚቀርብበትን ዋጋ ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል።

የሴቶችና የህጻናት ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ከውጭ ተመርተው ሲገቡ ቀደም ሲል ተጥሎባቸው የነበረው የ30 በመቶ ከፍተኛ የታክስ ምጣኔ ተቀንሶ ወደ 10 በመቶ ብቻ እንዲሆን መደረጉንም ሚኒስቴሩ ማስታወቁ ይታወሳል።