የአውስትራሊያው ጠ/ሚ የመደፈር ክስ ላቀረበችው ሴት ትኩረት በመንፈጋቸው ይቅርታ ጠየቁ

ታትሟል

የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን፤ በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ውስጥ የመደፈር ወንጀል ተፈፅሞብኛል ብላ ክስ ላቀረበችው የቀድሞ አማካሪ ትኩረት በመንፈጋቸው ይቅርታ ጠየቁ።

ብሪታኒ ሂጊንስ ወንጀሉ ተፈፅሞብኛል የምትለው በፈረንጆቹ 2019 ሲሆን በወቅት ሥራዬን አጣለሁ በሚል ፍራቻ እንደነበራት ትናገራለች።

የ26 ዓመቷ ሂጊንስ ባለፈው ሰኞ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብላ ደረሰብኝ ያለችውን ከተናገረች በኋላ የሃገሬው ሰው መነጋገሪያ ሆናለች።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥታቸው ለጉዳዩ ትኩረት በመንፈጉ ይቅርታ ጠይቀዋል።

ሴትዬዋ ያቀረበችውን ክስ ተከትሎ ፖሊስ እንደ አዲስ ምርመራ ማድረግ ጀምሯል።

የቀድሞ የፖለቲካ አማካሪ የነበረችው ሂጊንስ ደረሰብኝ ያለችውን ለሥራ አጋሮቿ በተናገረች ጊዜ ብዙዎች ትኩረት እንደነሷት ትናገራለች።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ "የብሪታኒ ጥሪ የማንቂያ ደወል ይሆናል ብዬ አስባለሁ" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ብሪታኒ በወቅቱ የ24 ዓመት ወጣት ነበረች። በመከላከያ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ውስጥ መሥራት ከጀመረች ጥቂት ሳምንታት ብቻ ናቸው የተቆጠሩት።

አንድ ምሽት ከሌሎች የሥራ አጋሮቿ ጋር በመሆን ለመጠጣት እንደወጡና በመደፈር ወንጀል የምትከሰው በዕድሜ ከሷ የላቀው የሥራ ባልደረባም አብሯቸው እንደነበር ትናገራለች።

እሷ እንደምትለው ደፈረኝ ያለችው ሰው ወደ ቤት ሊሸኛት ብትፈቅድለትም ወደ ሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ወሰዳት።

ብሪታኒ በወቅቱ ሰክራ እንደነበርና እንዲሁም እንቅልፍ ጥሏት እንደነበር ነገር ግን ስትነቃ ሰውዬው ወሲባዊ ጥቃት እያደረሰባት እንዳገኘችው ተናግራለች።

"ስነቃ እየደፈረኝ ነው። ማልቀስ ጀመርኩ። እንዲያቆም ነገርኩት" ስትል ቴን ለተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግራለች።

ሰውዬው ወዲያው ክፍሉን ለቅቆ እንደሄደ ከሳሿ ትናገራለች።

ብሪታኒ የደረሰባትን ለአሠሪዎቿ ብትናገርም ቢሮው ጉዳዩን ጣል ጣል በማድረግ ለመሸፋፈን እንደሞከረ ትገልፃለች።

ጥቃቱን አድርሷል ተብሎ የተጠረጠረው ግለሰብ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ተስፋ የተጣለበት ሰው ነው ትላለች ብሪታኒ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሴትዬዋ ቀጥተኛ ይቅርታ ካቀረቡ በኋላ በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የሚስተዋለው ባሕል ሊጤን ይገባዋል ብለዋል።

የአውስትራሊያ ፖለቲካ ለሴቶች የማይመች እንደሆነ በስፋት ይነገራል።

የብሪታኒ ታሪክ በተለየ ደግሞ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ያለውን መርዛማ ሴቶች ጠል ባሕል ያሳየ ነው ተብሏል።