ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሚየንማር ተቃዋሚዎች ላይ እንደተተኮሰ ተመድ ገለጸ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዑክ የሚየንማር የጸጥታ ኃይሎች ተቃዋሚዎች ላይ እንደተኮሱ ገለጹ። ይህም ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ ነው።
በጄኔቫ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት ልዑኩ ቶማስ አንድሪውስ የመፈንቅለ መንግሥቱን ጠንሳሾች ወቅሰዋል።
በአገሪቱ ያልተገቡ ድርጊቶች እየተፈጸሙ እንደሚገኙ የፎቶ ማስረጃ እንዳለም ጠቅሰዋል። ልዑኩ ሚየንማር ላይ የመሣሪያ ማዕቀብ እንዲጣልም ጠይቀዋል።
የወታደራዊ ኃይሉ ኃላፊ ተቃውሞ እንዲቆም ቢጠይቁም ለተከታታይ ቀናት ሰልፉ እንደቀጠለ ነው።
በሚየንማር የአንድነት ቀን ሲከበር ኃላፊው ጀነራል ሚን አውግ ህላግ "አገራዊ አንድነት ያስፈልገናል" ቢሉም ሕዝቡ አን ሳን ሱ ቺን ጨምሮ ሌሎችም አመራሮች ከቁም እስር እንዲለቀቁ እየጠየቀ ነው።
በሚየንማር የአንድነት ቀን ሲከበር ወታደራዊ ኃይሉ 55 የውጪ ዜጎችን ጨምሮ 23,000 ታራሚዎችን ከእስር ለቋል።
የአንድነት ቀን የሚከበረው እአአ በ1947 በአን ሳን ሱ ቺ አባት አማካይነት የተፈረመውን ስምምነት በማስታወስ ነው።
ስዛኣር ሳን የተባለ ተማሪና የመብት ተሟጋች ለቢቢሲ እንደተናገረው ታራሚዎች የተፈቱት ተቃዋሚዎች ላይ ጥቃት ሊያደርሱ ነው ብሎ ይሰጋል።
የተመድ ልዑክ እንዳሉት የድርጅቱ የሰብዓዊ መብት መርማሪዎች ሚየንማር ለመግባት ፍቃድ አላገኙም። ሆኖም ግን ተቃዋሚዎች ላይ ጥይት እንደተተኮሰ ማስረጃ ተገኝቷል።
ተመድ የቃል መግለጫ ከማውጣት በዘለለ የመሣሪያ ሽያጭ ላይ ማዕቀብ እንዲጥልና ወታደራዊ ኃላፊዎች የጉዞ ክልከላ እንዲወጣባቸውም ጠይቀዋል።
የሳምንቱ መባቻ ላይ ሚያ ትዌ ተዌ ካሂግ የተባለች የ19 ዓመት ወጣት በጥይት ጭንቅላቷን መመታቷ አይዘነጋም። ለሕይወቷ አስጊ ሁኔታ ውስጥም ትገኛለች።
ፓሊሶች ተቃዋሚዎችን ለመበተን ውሃ፣ የፕላስቲክ ጥይትና መሣሪያ ተጠቅመዋል።
አንድ የቀይ መስቀል ኃላፊ ለሮይተርስ እንደገለጹት ሦስት ሰዎች በፕላስቲክ ጥይት ጉዳት ደርሶባቸዋል።
አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አገሮች ሚየንማር ውስጥ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ መሪዎች እንዲለቀቁ እየጠየቁ ነው።
ወታደራዊ ኃይሉ የብሔራዊ ምርጫ ውጤት ተጭበርብሯል ብሎ መፈንቅለ መንግሥት ካካሄደ 12 ቀናት ተቆጥረዋል።
ወታደራዊ ኃይሉ ተቃዋሚዎችን የሚደግፍ ሲሆን፤ አዲስ ፓርላማ መመሥረት ጀምሯል። አን ሳን ሱ ቺ እና ሌሎች መሪዎች በቁም እስር ላይ ሲሆኑ፤ በሕግ ወጥ መንገድ አገር ውስጥ የገባ የራድዮ መገናኛ (ዋኪ-ቶኪ) በመያዝ ክስ ተመሥርቶባቸዋል።