የአልሸባብ ታጣቂዎች በሶማሊያ ሞቃዲሾ ውስጥ ጥቃት ፈጽመው ዘጠኝ ሰዎችን ገደሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ በሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ የአልሸባብ ታጣቂዎች ከሆቴሉ ጠባቂዎች ጋር ብርቱ የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸው ታውቋል።
ትናንት [እሁድ] አመሻሽ ላይ አፍሪክ በተባለውና በመዲናዋ በሚገኝ ሆቴል ላይ የደረሰው ጥቃት የተጀመረው አንድን መኪና በማቃጠል ነበር። በዚህ ጥቃትም አልሸባብ ከጀርባ ያለሁት እኔ ነኝ በማለት ኃላፊነቱን ወስዷል።
እስካሁን በጥቃቱ የደረሰው የጉዳት መጠን መታወቁን የፖሊስቃል አቀባይ የሆኑት ሳዲቅ አሊ ለሮይተርስ እዳረጋገጡት አራት ጥቃት አድራሾችን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች በጥቃቱ ተገድለዋል።
ከአልቃኢዳ ጋር ቁርኝት ያለው የአልሸባብ ቡድን በመንግሥት ላይ ተደጋጋሚ መሰል ጥቃት ያደርሳል።
አንድ ባለስልጣን እንዳረጋገጡት መኪናዋ ላይ ቀድሞ ፍንዳታ ተፈጸመ፤ ከዚያ የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሆቴሉ መግቢያ በመጠጋት ተኩስ ከፈቱ።
አንድ ሆቴሉ ውስጥ የነበረ የአይን እማኝ "ፍንዳታው ሲከሰት ሆቴሉ ውስጥ ነበርኩ። ግድግዳውን በሚገርም ሁኔታ ነበር ያንቀጠቀጠው። በጣም ፈርተንም ደንግጠንም ነበር" ብሏል ለሮይተርስ በሰጠው ምስክርነት።
ታጣቂዎቹ ጥቃት የፈጸሙት ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግለትና በዋናው አውሮፕላን ማረፊያ አጠገብ በሚገኘው ሆቴል ላይ ነው። ሆቴሉ በተለይ የሶማሊያ ባለስልጣናት መሰባሰቢያ በመሆን ይታወቃል።
አንድ የፖሊስ አባል እንዳሉት ጥቃቱ በደረሰበት ወቅት በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው የፓርላማ አባላት እና ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች በሆቴሉ ውስጥ ነበሩ።
በማሕበራዊ ሚዲያ የተለቀቁ ምስሎች እንደሚያሳዩት ከጥቃቱ በኋላ ሞቃዲሾ በከፍተኛ ጭስ ታፍና ነበር።
ከሟቾቹ መካከል የቀድሞው ወታደራዊ ጀኔራል ሞሐመድ ኑር አንዱ መሆናቸውን የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ፋርማጆ በትዊተር ገጻቸው ይፋ አድርገዋል።
ፕሬዝዳንቱ "በእዚህ አረመኔያዊ ጥቃት ሕይወታቸውን ላጡት የሶማሊያ ዜጎች ምሕረት እንዲያደርግላቸው ፈጣሪን እጠይቃለሁ፤ በሶማሊያ ወታደር ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ለነበራቸው ጀኔራል ሞሐመድ ኑር ሞትም ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶኛል" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, MOHAMED FARMAAJO TWITTER
ይህ ጥቃት የተፈጸመው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አልሸባባን እና ሌሎች ታጣቂ ቡድኖችን ለመዋጋት የሶማሊያ ጸጥታን ሲደግፉ ከነበሩት የአሜሪካ ወታደሮች መካከል ቢያንስ 700 የሚሆኑት ወደ አሜሪካ እንዲመለሱ ትዕዛዝ ከሰጡ ከሳምንታት በኋላ ነው።
በቀጣይ ወር ምርጫ ለማካሄድ እየተዘጋጀች ባለችው ሶማሊያ፣ የአሜሪካ ወታደሮች መውጣት ምናልባትም አለመረጋጋት ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋትን በብዙዎች ዘንድ አጭሯል።












