ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፓላንድ ጽንስ ማቋረጥ ላይ የተጣለውን ገደብ የሚቃወም ሰልፍ እየተካሄደ ነው
ፓላንድ ውስጥ ጽንስ ማቋረጥ ላይ ገደብ በመጣሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለሦስት ተከታታይ ቀናት የተቃውሞ ሰልፍ እያካሄዱ ይገኛሉ።
ጽንስ ማቋረጥ የሚቻለው አንዲት ሴት ተደፍራ ከጸነሰች፣ በቤተሰብ መካከል የግብረ ስጋ ግንኙነት ከተፈጸመ ወይም እርግዝናው የእናቲቱን ሕይወት አደጋ ውስጥ ከከተተ ብቻ ነው የሚለውን አዲስ ሕግ በርካቶች እየተቃወሙ ነው።
በፖላንድ የኮኖናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የወጣውን ክለከላ አፍርስው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ሕጉ ባለፈው ሐሙስ ከተላለፈ በኋላ ነው ሰልፍ መካሄድ የጀመረው። አብዛኞቹ የፓላንድ ዜጎች ጽንስ ማቋረጥ ላይ የሚጣል ጥብቅ እገዳን ይቃወማሉ።
በመዲናዋ ዋርሳው ሰልፍ ያካሄዱ ዜጎች "ነጻነት፣ እኩልነት፣ ጽንስ ማቋረጥ ሲያስፈልግ ይፈቀድ" ሲሉ መፈክር አሰምተዋል።
"መንግሥቴ እየገደለኝ ነው" "የኔ ሰውነት የኔ ምርጫ" "አብዮቱ ማህጸን አለው" የሚሉ መፈክሮችም ታይተዋል።
እአአ በ1993 የወጣ መመሪያ መፍትሔ ሊገኝላቸው በማይችል የጤና ችግሮች ወቅት ጽንስ እንዲቋረጥ መፍቀዱ ሕገ ወጥ እንደሆነ ዘንድሮ ጥቅምት ላይ የፓላንድ ፍርድ ቤት ወስኗል።
በ2019 በአገሪቱ 98% የሚሆን ጽንስ የተቋረጠው ይህን ሕግ መሠረት በማድረግ ነበር።
አዲሱ ሕግ ጽንስ የማቋረጥ መብትን የሚደግፉ ዜጎችን አስቆጥቷል።
ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው የፓላንድ ወግ አጥባቂ መንግሥት ሕጉን ይደግፋል።
ፍርድ ቤቱ "ያልተወለደ ልጅም የሰው ልጅ ነው። ስለዚህ በፓላንድ ሕግ መጠበቅ አለበት" ሲል አዲሱን ሕግ ተከላክሏል።
በሌላ በኩል ይህ ሕግ የጸደቀበትና በሂደቱ የተሳተፉ ሰዎች ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ተቃዋሚዎች አሉ።
የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ክዝይስቲፍ ሶቦልስኪ የተቃውሞ ሰልፉ የኮቪድ-19 መከላከያ መርህን የጣሰ ስለሆነ ሕገ ወጥ ነው ብለዋል።