ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሆሊውዱ ሐርቪይ ዋይንስቲን ንብረት የጾታ ጥቃት ላደረሰባቸው እንዲከፋፈል ተወሰነ
በርካታ ሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት በማድረስ የተከሰሰውና በኋላም ዘብጥያ የወረደው የሆሊውድ ሥመ ጥር ፕሮዲውሰር ሀርቪይ ዋይንስቲን ኩባንያ ገንዘብ ለተጠቂዎች እንዲከፋፈል ተወሰነ።
ይህ ኩባንያው ኪሳራ በማወጅ እየከሰመ የነበረ ድርጅቱ ሲሆን ዋይንስቲን ኮ በሚል ይታወቃል።
ኩባንያው ኪሳራ አውጆ ሲከስም የሚቀረው ገንዘብ ለጥቃት ሰለባዎቹ እንዲከፋፈል ነው የተወሰነው።
በአሜሪካ ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ ይህ ከኩባንያው መክሰም በኋላ የተገኘው 17 ሚሊዯን ዶላር ገንዘብ ለሰለባዎቹ እንዲከፋፈል ፈቅደዋል።
የ68 ዓመቱ ዋይንስቲን ባለፈው ዓመት ነበር ተከሶ የ23 ዓመት እስር የተፈረደበት።
ጾታ ጥቃት ላደረሰባቸው ሴቶች የሚከፋፈለው 17 ሚሊዮን ዶላሩ ዊንስቴን ካምፓኒ በኪሳራ መክሰሙን ተከትሎ የመጣ ነው። ይህ ኩባንያው ኪሳራ ያወጀው በፈረንጆቹ 2018 ነበር።
'ዋይንስታይን ኮ' ኩባንያ የተመሰረተው ራሱን የቻለ የፊልም ስቱዲዮ ሆኖ ሲሆን ከመሥራቾቹ አንዱ ባለድርሻ በወሲብ ቅሌት ዘብጥያ የወረደው ሐርቪ ዋይንስታይን ነበር።
ይህ ስመ ጥር ኩባንያው መሽመድመድ የጀመረው በ2017 መጨረሻ የሐርቪይ ዋይንስታይን ስም መጠልሸት መጀመሩ ተከትሎ ነበር።
ሐርቪይ በዚያ ወቅት የቀድሞ ረዳቱንና አንዲት ሌላ ተዋናይትን በመድፈር ክስ ቀርቦበት ነበር።
አሁን በዚህ ኩባንያው መክሰም የተገኘው የ17 ሚሊዮን ዶላር ገቢ 50 ከሳሾቹ የሚከፋፈሉት ነው የሚሆነው።
ይህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ከሳሾቹ ድምጽ እንዲሰጡበት ከተደረገ በኋላ ሲሆን 39 ከሳሾቹ ገንዘቡን ለመከፋፈል ፈቅደው ድምጽ ሰጥተዋል። ስምንቱ ግን ተቃውመዋል።
ይህ ግዙፍ የነበረው የዋይነስቲን የፊልም ኩባንያ ንብረቱን ለላንቴርን ኢንተርቴይመንት የሸጠ ሲሆን ይህም በኋላ ስፓይግላስ ሚዲያ ግሩፕ የሆነው ነው።
የዋይንስተን ኩባንያ ኪሳራ ላይ ከመውደቁ በፊት ንብረቶቹን ለዚህ ኩባንያው ያስተላለፈው በ289 ሚሊዮን ዶላር ነበር።