737 ማክስ አውሮፕላኖችን ወደ በረራ እንዲመለሱ መፍቀድ 'አደጋ አለው' ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሲያትል አሜሪካ የቦይንግ 737 አውሮፕላን ማምረቻ ፋብሪካ ውስጥ ከፍተኛ የሥራ አመራር የነበሩት ግለሰብ በኩባያው ምርት 737 ማክስ አውሮፕላን ደኅንነት ላይ ያላቸውን ስጋት ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ላየን አየር መንገድ ንብረት የነበሩት ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ተከስክሰው በድምሩ 346 ሰዎች ካለቁ በኋላ አውሮፕላኑ በረራ እንዳያደርግ ለሁለት ዓመታት ታግዶ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በአውሮፕላኖቹ ላይ የምህንድስና ማሻሻያ ተደርጎባቸው የብቃት ፍተሻ ተደርጎላቸው ነበር፡፡
ይህን ተከትሎም በብራዚል እና ሰሜን አሜሪካ በረራ እንዲያደርግ ፍቃድ ተሰጥቷቸዋል።
ይሁን እንጂ የቀድሞ በፋብሪካው ቁልፍ የሥራ አመራር የነበሩት ኤድ ፒርሰን በቅርቡ ይፋ ባደረጉት ሪፖርት በማክስ 737 አውሮፕላን ላይ የኤሌክትሪካል ችግሮች እና በማምረቻ ፋብሪካ ውስጥ የምርት ጥራት ችግር አሁንም ሊፈተሽ የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል።
በአሜሪካ እና አውሮፓ የሚገኙ የአውሮፕላን ደኅንነት ተቆጣጣሪዎች ግን በ737 ማክስ አውሮፕላን ደኅንነት ላይ ያደረግነው ምርመራ ጥልቅና ዘርዘር ያለ ነው በማለት የአውሮፕላኑ የደኅንነት ሁኔታ አሁን ላይ እንደማያሳስብ ይናገራሉ።
አውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ለአደጋዎቹ ምክንያት የነበረውን ሥርዓት ማሻሹሉን አስታውቋል።
የአሜሪካው ፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር በበኩሉ ሁለቱ አደጋዎች በፋብሪካው ካለ የምርት ጥራት ችግር ጋር የሚያገናኘው ነገር አለመኖሩን እና እያንዳንዱ አውሮፕላን ለገዢው ከመተላለፉ በፊት በአቪዬሽኑ አስተዳደር ሠራተኞች ፍተሻ እንደሚያካሂድ ተናግረዋል።
ኤድ ፒርሰን ግን ተቆጣጣሪዎች እና መርማሪዎች ሁለቱ የአውሮፕላን አደጋዎች እንዲከሰቱ ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን አልተመለከቱም ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኤምካስ ችግር
የኢንዶኔዢያው ላየን ኤርዌይስ 737 ማክስ አውሮፕላን የበረራ ቁጥር JT610 ከጃካርታ በተነሳ በደቂቃዎች ውስጥ በጃቫ ባሕር ውስጥ ተከሰከሰ።
ከአምስት ወራት በኋላ ተመሳሳዩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ለመብረር በተነሳ በደቂቃዎች ውስጥ ተከስክሷል።
ከእነዚህ አደጋዎች ጋር በተያያዘ የአውሮፕላኑ የደኅንነት መጠበቂያ የምህንድስና ሥርዓት የሚደረገው ምርምራ ዋነኛው ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል።
ኤምካስ አውሮፕላኑን በከፍተኛ ሁኔታ ወደላይ እንዳይወጣ ወይም ወደታች እንዳያሽቆለቁል ለመቆጣጠር እንዲቻል ተብሎ የተሠራ ሥርዓት ነው።
አውሮፕላኑ ዝግ ሲል በትክክለኛው ከፍታ እንዲበር ለማስቻል የሚፈለገውን ኃይል ለማግኘት ወደ ላይ ወይም ቁልቁል በመሄድ ወደሚፈለገው ከፍታ ይመለሳል።
ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን በአውሮፕላኑ ክንፎች በኩል ያለውን የመቆጣጠሪያ አቅም በመቀነስ አውሮፕላኑ እንዲወድቅ ሊያደርገው ይችላል።
አደጋው በደረሰበት ቦይንግ 737 ማክስ ዓይነት አውሮፕላኖች ላይ ያለው የመቆጣጠሪያ ሥርዓት (ኤምካስ) ግን እንዲህ አይነቱ ሁኔታ ሲከሰት አውሮፕላኑን እራሱ አስተካክሎ ወደ ትክክለኛው እንዲመልስ ሥርዓቱ ራስ በራሱ እርምጃ ይወስዳል።
በሁለቱ አደጋ ወቅት አብራሪዎቹ አውሮፕላኑ ከፍታ እንዲያገኝ በሚጥሩበት ወቅት ይህ ስርዓት ግን የአውሮፕላኑ አፍንጫ ቁልቁል እንዲሆን በተደጋጋሚ ሲያስገድድ ነበር።
የማክስ 737 አውሮፕላኖችን ደኅንነት ለማረጋገጥ የኤምካስ ሥርዓትን ደግም ዲዛይን የማድረግ ሥራ ላይ አተኩሮ ቆይቷል።
ለቀድሞው የቦይንግ የሥራ አመራር ኤድ ፒርሰን ግን ይህ በቂ አይደለም።
ኤድ በቦይንግ ፋብሪካ ያለው የምርት ጥራት ጉድለት እጅጉን እንደሚያሳስበው እና አውሮፕላኑን ወደ አገልግሎት ለመመለስ በሚደረገው ጥድፊያ ያሉት ችግሮች በቂ መፍትሄ እስካልተሰጣቸው ድረስ ይህን አውሮፕላን ወደ ሥራ መመለስ አደጋ አለው ይላል።
የኤድ ፒርሰን ሪፖርት በአቪዬሽን ዘርፉ የከበረ ስም ባላቸው ግለሰቦችም ድጋፍ አግኝቷል። ከእነዚህም መካከል የቀድሞ ዝነኛ አብራሪ ካፒቴን ቼስሊ ሰለንበርገር ይገኙበታል።
ይህ አብራሪ እአአ 2009 ላይ በበረራ ላይ ሳለ ሞተሩ የተበላሸ ኤርባስ አውሮፕላን በማንሃተን ሀድሰን ወንዝ ላይ በማሳረፍ የበርካቶችን ሕይወት በመታደጉ ሲወደስ የኖረ ካፒቴን ነው፡፡
ይህ ዝነኛ አብራሪ ለ737 ማክስ አውሮፕላን የተደረገው ማሻሻያ በቂ አይደለም ሲል ስጋቱን ተናግሯል፡፡
አብራሪው 737 ማክስ አውሮፕላን ላይ የተገጠመው የአደጋ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ኋላ ቀር ነው፤ ብዙ መመለስ ያለባቸው ጥያቄዎች አሉ፤ እነዚህን አውሮፕላኖች ወደ ሥራ መመለስ አደጋ አለው ይላል።












