የጄምስ ቦንድ ፊልም ለዕይታ የሚበቃበት ጊዜ ተራዘመ

ኬሪ ጆጂ ፉኩናጋ እና ዳንኤል ክሬግ

የፎቶው ባለመብት, Bonhams

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አዲሱ የጄምስ ቦንድ ፊልም ለዕይታ የሚበቃበት ቀን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለሶስተኛ ጊዜ ተራዘመ።

ኖ ታይም ቱ ዳይ (No Time To Die) የተሰኘው ይህ ፊልም ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ የተገፋ ሲሆን አሁን በመጪው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ለዕይታ እንደሚበቃ ከፊልሙ ድረ ገጽ ማወቅ ተችሏል።

ከዚህ ቀደም ለዕይታ ይበቃል ተብሎ የነበረው ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ ነበር።

ፊልሙ ጄምስ ቦንድን በዓብይ ገጸ ባህሪነት በመሳል ለዓለም ሕዝብ ሲያስኮመኩም 25ኛው ሲሆን እንግሊዛዊው እና የብሪቴይን 007 የደህንነት ባለሙያ ወይንም ሰላይ ሆኖ የሚሰራው ዳንዔል ክሬግ ደግሞ ለመጨረሻ ጊዜ በፊልሙ ላይ መተወኑ ነበር።

በፊልሙ ላይ ሊያ ሴይዱክስ እና ራሚ ማሌክ ተሳትፈውበታል።

ፊልሙ ለዕይታ የሚበቃበት ጊዜ መራዘሙ ይፋ መሆኑ ለሲኒማ ቤቶች በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባቸዋል።

አስቀድሞም ሲኒማ ቤቶች በእንቅስቃሴ ገደቡ ተዘግተው የቆዩ በመሆኑ የተመልካች ድርቅ የመታውን አዳራሻቸውን በእንዲህ ዓይነት ፊልሞች ለማነቃቃት ቋምጠው እየጠበቁ ነበር።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የፊልም ሰሪዎች አውራ የሚባለው ዳኒ ቦይል እና ሰር ስቲቭ ማክክቂን ለዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ለሲኒማ ቤቶች የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ የሚጠይቅ ደብዳቤ አስገብተዋል።

እነዚህ ባለሙያዎች የዩኬ ሲኒማ "በገደል አፋፍ ላይ ይገኛል" ሲሉ ደብዳቤውን ለመጻፍ ያበቃቸውን ምክንያት ገልፀዋል።

የቦንድ ፊልም ለዕይታ የሚበቃበት ጊዜ መዘግየት ሌሎች ትልልቅ ፊልሞች ለዕይታ ወደ ተመልካች የሚመጡበትን ጊዜ እንዲገፉ አድርጓቸዋል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከዘገዩት ፊልሞች መካከል የቶም ክሩዝ ቶፕ ገን፡ ማቭሪክ ኤንድ ማርቭልስ ብላክ ዊዶው ይገኝበታል።

ራሚ ማሌክ

የፎቶው ባለመብት, Universal

ሶኒ ጎስት በስተርስ፣ አፍተር ላይፍ፣ ፒተር ራቢት 2፣ ቶም ሆላንድ አንቻንትድ እና ሲንደሬላ እንዲሁም ሌሎቹ ፊልሞቹ ለዕይታ የሚበቁበትን ቀን ሲገፋ ዩኒቨርሳል በበኩሉ የቶም ሃንክስ ግለ ህይወት ላይ የሚያተኩረውን ፊልም ከሚያዚያ ወደ ሚቀጥለው ዓመት ሕዳር አሸጋግሮታል።

የዩኬ የሲኒማ ማህበር ኖ ታይም ቱ ዳይን በድጋሚ ወደ ሌላ ጊዜ ማስተላለፍን በተመለከተ ሲናገር "የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሁናቴ በዩኬ፣ በአሜሪካ እና በሌሎች ፊልም በሚታይባቸው ትልልቅ ስፍራዎች ካለው ሁኔታ አንጻር የሚጠበቅ ነው፤ ነገር ግን በግልጽ ያሳዝናል።"

የጄምስ ቦንድም ሆኑ ሌሎች ፊልሞች ለዕይታ የሚበቁበት ጊዜ መገፋት ለዩኬ የሲኒማ ዘርፍ ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ማሳያ ነው ሲልም አትቷል።

አክሎም መንግሥት ሲኒማ ለሚያሳዩ "በቀጥታ ድጋፍ" እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የጄምስ ቦንድ ፊልም ለሶስተኛ ጊዜ መተላለፍ ሌላ ስጋትም አጭሯል።

ፊልሙ ሲኒማ ቤቶችን ገሸሽ አድርጎ በኦንላየን ተጠቃሚዎች ሊመጣ ይችላል የሚሉ ወሬዎች መናፈስ ጀምረዋል።

ከዚህ ቀደም በድጋሚ የተሰራው ሙላን እንዲሁም ፒክሳርስ ሶልስ በሲኒማ መታየታቸውን ትተው ዲዝኒ ፕላስ በተሰኘ የኦንላየን ፊልም መመልከቻ በኩል መጥተዋል።

ወንደር ውመን 1984 በአሜሪካ በኤችቢኦ ማክስ እየታየ ነው። ሌሎች ፊልሞችም ይህንን ልምድ ተከትለው በኦንላየን ባሉ አማራጮች በኩል እንደሚታዩ ከተሰማ በኋላ በሆሊውድ እና በአሜሪካ የሲኒማ ማሳያዎች መካከል ውጥረት ተፈጥሯል።

በርግጥ የጀምስ ቦንድ ፊልም ቃል እንደገባው በሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት ወር በሲኒማ መታየት ከጀመረ በ2015 ለዕይታ ከበቃው ፊልም ስድስት ዓመት በኋላ ይታያል ማለት ነው።

በ2015 ለሕዝብ ይፋ የሆነው የጄምስ ቦንድ ፊልም ከቦክስ ኦፊስ 900 ሚሊዮን ዶላር አግኝቷል።

የ YouTube ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን Google YouTube ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በGoogle YouTube. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የGoogle YouTube ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ YouTube ይዘት መጨረሻ