የአውሮፓ ሕብረት በትግራይ ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲመቻች ጠየቀ

ታትሟል

የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ከተወያዩ በኋላ በሁሉም የትግራይ ክልል አካባቢዎች የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መስመር እንዲመቻች ጠየቁ።

የእርዳታ ድርጅቶች ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የክልሉን አንዳንድ አካባቢዎች አንዲጎበኙ የተፈቀደላቸው ቢሆንም ይህ ከህወሓት ጋር ውጊያዎች የተካሄዱባቸውን ሁሉንም የክልሉን አካባቢዎች የሚያካትት አይደለም ተብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ በምግብ አቅርቦት እጥረትና በዘረፋ ሳቢያ አሳሳቢ ነው ሲል ገልጾታል።

የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊው ጆሴፍ ቦሬል በትግራይ ክልል ውስጥ ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መስመር መመቻቸት አለበት ብለዋል።

ኃላፊው ጨምረውም ይህ ለኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበ ጥያቄ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት መፈጸም ያለበት አስፈላጊ እርምጃ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት በትግራይ ክልል ውስጥ ያሉና ኤርትራዊያን ስደተኞችን የሚያስጠልሉ ሁለት የስደተኛ ካምፖችን ለመጎብኘት እንዳልቻለ ማመልከቱ ይታወሳል።

የስደተኛ ካምፖቹን የሚያሳዩ የሳተላይት ምሰሎች የዓለም ምግብ ፕሮግራም ህንጻን ጨምሮ በካምፖቹ ውስጥ የሚገኙ ቤቶች መውደማቸውን አመልክተዋል ተብሏል።

በቅርቡ አንድ ወታደራዊ አዛዥ የኤርትራ ወታደሮች ኢትዮጵያ ውስጥ መግባታቸውን ያመኑ ሲሆን የኤርትራ ሠራዊት አባላት የተለያዩ በደሎች ፈጽመዋል በሚል በርካታ ክሶች ሲሰነዘሩባቸው ቆይቷል።

የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ከገባች በኋላ በነበረው ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት ጋር የሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ የሚያስችሉ መስመሮችን ለማመቻቸት ከስምምነት መድረሱ ይታወሳል።

ነገር ግን አሁን ድረስ የእርዳታ ድርጅቶች በግጭቱ ሳቢያ ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጠው ለቆዩ የክልሉ ነዋሪዎችና በካምፖች ለሚገኙ ስደተኞች አስፈላጊውን የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችላቸው ያልተገደበ ፈቃድ እንዲሰጣቸው እየጠየቁ ይገኛሉ።

በህወሓት ኃይሎችና በፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት መካከል የተቀሰቀሰውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ የትራንስፖርትና ኮምዩኒኬሽን ግንኙነት መስመሮች በክልሉ ውስጥ ተቋርጠው የቆዩ ሲሆን፤ መቀለ ከተማ ከተያዘች በኋላ መንግሥት በጦርነቱ የተጎዱ መሰረተ ልማቶች ተጠግነው ክልሉን ክፍት እንደሚደረግ ገልጾ ነበር።

የአውሮፓ ሕብረት፣ የተባበሩት መንግሥታትና የተለያዩ የተራድኦ ድርጅቶች በትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ስለሚገኙ መንግሥት የእርዳታ አቅርቦት መስመሮችን እንዲያመቻች እየጠየቁ ነው።

በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች ጦርነቱን ሸሽተው ወደ ሱዳን መግባታቸው የተነገረ ሲሆን በክልሉ ውስጥ ያሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል።

ይህ ቀውስ የተከሰተው የትግራይ ክልልን ያስተዳድር የነበረው የህወሓት ኃይሎች በአገሪቱ ሠራዊት የሠሜን ዕዝ ላይ በጥቅምት ወር መጨረሻ አካባቢ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ በተቀሰቀሰ ወታደራዊ ግጭት ሳቢያ ነው።