ሪፐብሊካኗ ሎረን ቦይበርት ሽጉጥ ይዘው ወደ ኮንግረስ ሊገቡ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አዲስ የተመረጡት የኮንግረስ አባል በዋሽንግተን ዲሲ የሥራ ዘመናቸው የእጅ ሽጉጣቸውን ይዘው ለመሳተፍ ቃል ገቡ፡፡
እሁድ ዕለት በተለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል የሪፐብሊካኑ ሎረን ቦይበርት በከተማው ከመዞራቸው በፊት ሽጉጣቸው ላይ ጥይት ሲጭኑ ታይተዋል።
ከሁለት ሚሊዮን ጊዜ በላይ እይታ በነበረው ቪዲዮ "መሳሪያዬን ወደ ዲሲ [ዋሽንግተን ዲሲ] እና በኮንግረስ ይዤ እገኛለሁ" ብለዋል።
የከተማው የፖሊስ አዛዥ መሳሪያን ስለመያዝ በወጣው ጥብቅ ህግ ዙሪያ ከቦበርት ጋር ለመነጋገር ማቀዳቸውን ተናግረዋል።
ቦይበርት በኮሎራዶ ራይፍል ከተማ፣ ሹተርስ ግሪል የተባለ ምግብ ቤት ሲኖራቸው በአካባቢው ህግ መሠረት የምግብ ቤቱ ሠራተኞች በግልጽ መሣሪያ እንዲይዙ ያበረታታሉ።
ባለፈው ሕዳር ወር በተካሄደው ምርጫ የጦር መሣሪያ መብት ጉዳይ የዘመቻቸው ቁልፍ አካል ነበር፡፡
እሁድ በትዊተር በተለቀቀው ቪዲዮ ቦበርት "በአሜሪካ በጣም ነጻ ከሆኑ ከተሞች በአንዱ ብሠራም መብቶቼን አሳልፌ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆንም" ብለዋል።
"ካለኝ ቁመት እና ሰውነት አንጻር በሕጋዊ መንገድ ራሴን ለመጠበቅ እመርጣለሁ፤ ምክንያቱም የእኔ የራሴ ምርጥ ጠባቂ ነኝ" ብለዋል።
ስለጉዳዩ ፖሊስ ፈጣን ምላሽ የሰጠ ሲሆን የዋሽንግተን ዲሲ የፖሊስ አዛዥ ሮበርት ኮንቴ ለጋዜጠኞች "የኮንግረንስ አባል ቢሆኑም በዲሲ ጎዳናዎች ላይ ከነመሣሪያቸው ከተያዙ እንደ ማንኛውም ሰው ተመሳሳይ ቅጣት ይደርስባቸዋል" ብለዋል።
የአሜሪካ ህገ-መንግስት የህዝብን መሳሪያ የመያዝ መብትን የሚያረጋግጥ ቢሆንም ይህንን የሚመለከቱ ህጎች ከግዛት ግዛት ይለያያሉ።
የኮንግረስ አባላት መሳሪያዎቻቸው ጥይት እስካልጎረሱ ድረስ በቢሮዎቻቸው ውስጥ እንዲያስቀምጡ እና በዋሺንግተን ዲሲ እንዲያጓጉዙ ይፈቀድላቸዋል።
ሆኖም መሣሪያውን በከተማው ጎዳናዎች ለማጓጓዝ ፈቃድ የሚያስፈልግ ሲሆን ከሌሎች ግዛቶች የሚመጡ መሳሪያዎች መጀመሪያ መመዝገብ አለባቸው።
ባለፈው ወር የዲሞክራቲክ ፓርቲ ሴናተሮች ቡድን የኮንግረስ አባላት ነባር ህጎችን ለማጥበቅ አዲስ ህግ እንዲጸድቅ አቅርበዋል፡፡












