ሳዑዲ የሴቶች መብት ተሟጋቿ ላይ የአምስት ዓመት እስራት ፈረደች

ሉጂን አልሀትሉል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ታዋቂዋ የሳዑዲ የሴቶች መብት ተሟጋች ሉጂን አልሀትሉል የአምስት ዓመት ከስምንት ወር እስራት ተፈረደባት። የመብት ተሟጋቿ በተለይም ሴቶች መኪና እንዲነዱ ንቅናቄ በማድረግ ትታወቃለች።

የ31 ዓመቷ ሉጂን ላለፉት 2 ዓመታት ተኩል ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግበት ማረሚያ ቤት ውስጥ ቆይታለች። እሷና ሌሎችም የመብት ተሟጋቾች እአአ በ2018 ነበር የታሰሩት።

ከሳዑዲ አረቢያ ጠላቶች ጋር ንግግር ማድረግና ሌሎችም ክሶች ተመስርተውባቸዋል።

ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች እስረኞቹ እንዲለቀቁ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ነበር። ሆኖም ግን የሳዑዲ ልዩ የወንጀል ፍርድ ቤት የመብት ተሟጋቿ ላይ እስር ፈርዷል።

የአገር ክህደት ጉዳዮችን ለመዳኘት የተቋቋመው ፍርድ ቤቱ፤ የመብት ተሟጋቿ ላይ ውሳኔ ያሳለፈው ብሔራዊ ደህንትን አደጋ ላይ ለመጣል እና የውጪ አገሮችን አጀንዳ ለማስፈጸም ሞክራለች ብሎ ነው።

ከተፈረደባት የአምስት ዓመት ከስምንት ወር እስራት ላይ ሁለት ዓመትና አስር ወር እንደተነሳላት ፍርድ ቤቱ አስታውቋል።

ሉጂንም ሆነች ቤተሰቧ ክሱን አይቀበሉም። ማረሚያ ቤት ሳለች እንግልት እንደደረሰባት ቢከሱም ፍርድ ቤቱ አጣጥሎታል።

የመብት ተሟጋቿ የታሰረችው የሳኡዲ ሴቶች መኪና እንዲነዱ ከመፈቀዱ ከሳምንታት በፊት ነበር። ንቅናቄውን ከመሩት አንዷ ስትሆን፤ የሳኡዲ መንግሥት ግን እስሯ ከንቅናቄው ጋር አይገናኝም ይላል።

ከታሰረች በኋላ ለሦስት ወራት ከሰዎች ጋር እንዳትገናኝ እንደታገደች እንዲሁም የኤሌክትሪክ ንዝረት፣ ድብደባና ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባት ቤተሰቦቿ ይናገራሉ። እንግልት አልደረሰብኝም ካለች ነጻ እንደምትወጣ እንደተነገራትም ቤተሰቧ ገልጿል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የፍርድ ሂደቱ ዓለም አቀፍ አሠራርን አልተከተለም ይላሉ።

ጥቅምት ላይ ወደ ልዩ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት መወሰዷን አምንስቲ ተቃውሞ ነበር።

የመታሰሯ ጉዳይ ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢል ሰልማንን ከሚያስተቹ ሁነቶች አንዱ ነው። ሴቶች መኪና እንዳይነዱ የሚከለክለውን ሕግ በማንሳትና ወግ አጥባቂዋን ሳኡዲ ለኢንቨስትመንት ክፍት በማድረግ ተራማጅ መሪ ቢባሉም፤ የመብት ተሟጋቾች መታሰር ግን በእጅጉ አስኮንኗቸዋል።

የጋዜጠኛ ጀማል ካሾግጂ ግድያ ጉዳይም ልዑል አልጋ ወራሹ ከሚወቀሱባቸው አንዱ ነው።

ሉጂን የሰብአዊ መብት ትግል ተምሳሌት እየሆነች መጥታለች። ሴቶች መኪና እንዲያሽከረክሩ ንቅናቄ ስታደርግ ከነበረበት ጊዜ በበለጠ ከታሰረች በኋላ ከፍተኛ እውቅናን አግኝታለች።

ጆ ባይደን በይፋ ሥልጣን ሲረከቡ የሳኡዲ የሰብአዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ ጥብቅ እርምጃ ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሆኖም ግን ሳዑዲ የራሷን አቅጣጫ ከመከተል ወደኋላ የምትል አይመስልም። የዓለም ቁጥር አንድ የነዳጅ አምራች መሆንና የቀጠናውን የበላይነት መያዝ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ላይ ጫና እንደሚያሳድር ታምናለች።

ሉጂን ከዚህ ቀደም የታሰረችበት ጊዜ ተቆጥሮ የተፈረደባትን እስር አጠናቃ በቅርብ ትወጣለች ተብሎ ይታመናል።

ይህም ሳዑዲ የሚያድርባትን ጫና ይቀንስ ይሆናል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ሳኡዲ አረቢያ ሴቶች እንዲያሽከረክሩ ሕግ ብታረቅም ጠያቂዎቹን ግን እስር ቤት አግዛቸዋለች