ፍትህ ፡ በኦሮሚያ ክልል ባሕላዊ ፍርድ ቤት ሊቋቋም ነው

ታትሟል

የኦሮሞ ሕዝብ በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የሚገጥሟቸውን እክሎች ማለትም የቤተሰብ እና የጎረቤት፣ እንዲሁም የጎሳ ግጭትን ከዘመናዊ ሕግ በተጨማሪ በሽምግልና ይፈታል።

ሽማግሌም ግራ ቀኙን ካዳመጠ በኋላ ጉዳዩን መዝኖ ያጠፋው እንዲቀጣ፣ የተጎዳው ደግሞ እንዲካስ ይወስናል።

የኦሮሚያ ክልልም ይህንን ማኅበረሰቡን ግጭቶችንና ችግሮችን ሲፈታበት የቆየውን እሴት የሕግ እውቅና ባለው መንገድ እንዲሰራ ለማድረግ ባሕላዊ ፍርድ ቤት እያቋቋመ መሆኑን የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ገልጿል።

በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኮሙኑኬሽን ጉዳዩች ዳይሬክተር አቶ ጎንፋ አቶማ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ይህ የሚቋቋመው ባሕላዊ ፍርድ ቤት በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ላይ ያለውን ጫና የሚያቃልል ይሆናል።

"ባሕላዊ ፍርድ ቤት ማለት በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን ባሕላዊ እሴት በመጠቀም ግጭቶቹን በፍርድ ቤት መፍታት ማለት ነው። ፍርድ ቤቱ የሚጠቀማቸው የመደበኛ ፍርድ ቤቶችን ሕግ ሳይሆን ባሕላዊ ሕጎችን ነው።"

የዚህ ባሕላዊ ፍርድ ቤት አመሰራረትም የፌደራል እና የኦሮሚያ ክልልን ሕገ መንግሥትንና እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች ምሥረታ እና ሥልጣን ድንጋጌ 216/11 መሰረት ያደረገ መሆኑን አክለው ገልፀዋል።

ይህ ባሕላዊ ፍርድ ቤት በኦሮሞ እሴትና በገዳ ሥርዓት ላይ በመመስረት የሚሰራ ስለሆነ ለማኅበረሰቡ ባሕል መጎልበት የሚኖረው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም ይላሉ ዳይሬክተሩ።

በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ፍርድ ቤቶች በዓመት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የክስ መዝገቦችን ያስተናግዳሉ። ይህንን ባሕላዊ ፍርድ ቤት ለማቋቋም በተካሄደ ጥናት የኦሮሞ ባሕል ተጠናክሮ ባለባቸው አካባቢዎች የክስ መዝገቦች ቁጥር አናሳ መሆኑ መስተዋሉን አቶ ጎንፋ ይናገራሉ።

እንደምሳሌም በቦረና ዞን፣ ጎዳዮች በባሕላዊ መንገዶች በሚፈቱበት አካባቢ የክስ መዛግብት አነስተኛ ናቸው። በሁሉም የቦረና ወረዳዎች በዓመት የሚታዩ ክሶች በሌሎች አካባቢ በአንድ ወረዳ ከሚታዩት መዝገቦች በታች ናቸው ሲሉ ያነጻጽራሉ።

"ይህ ባሕላዊ ፍርድ ቤትም፣ የራሱ የሆነ መዋቅር ያለው ሽምግልና ነው፤ በቀበሌና በወረዳ ደረጃ የራሱ መዋቅሮች ይኖሩታል፤ የራሱ የሆነ ሥርዓት ዘርግቶ ባለመኖሩ ብቻ ነው ከሽምግልና ለየት የሚያደርገው" ብለዋል።

ከመደበኛው ፍርድ ቤት ጋር የሚኖረውን ግንኙነት በተመለከተም ሲያስረዱ፣ ጉዳዩ በባሕላዊ ፍርድ ቤት ሲታይ የነበረ በይግባኝ ሂደት ወደ መደበኛው ፍርድ ቤት መተላለፍ እንደሚችል ይናገራሉ።

"በቀበሌ ደረጃ በባሕላዊ ፍርድ ቤት የሚታይ ጉዳይ በይግባኝ ወደ ወረዳ ባሕላዊ ፍርድ ቤት ሊሄድ ይችላል፤ ከዚህ አልፎ የተሰጠው ውሳኔ የሕግ ግድፈት ያለው ከሆነ ወደ ወረዳ መደበኛው ፍርድ ቤት በመወሰድ ይታያል" ብለዋል።

በዚህ ባሕላዊ ፍርድ ቤት የሚሰሩት የሕግ ባለሙያዎች የሕግ ትምህርትን የተማሩ የሕግ ባለሙያዎች ሳይሆኑ የገዳ ሥርዓትና ባሕልን የሚያውቁ ሽማግሌዎች ናቸው።

አባገዳዎች ምን ይላሉ?

የቱለማ አባ ገዳ ጎበና ሆላ ኦሮሞ ከጥንት አንስቶ በባሕላዊ እሴትና ሕግጋቶች የሚገጥሙትን ማኅበራዊ ችግሮች ሲፈታ እንደኖረ ይናገራሉ።

አሁን ሊመሰረት ያለው የባሕላዊ ፍርድ ቤት በገዳ ሥርዓት ውስጥ የነበረውና ማኅበረሰቡ ችግሩን ሲፈታባቸው የነበሩትን እሴቶች መልሶ የሚያጠናክር ነው ሲሉም ያስረዳሉ።

"ኦሮሞ የራሱን ሕግጋቶች በመቅረጽ ይተዳደር ነበር። አሁን ዘመናዊነት ተስፋፍቶ በዘመናዊ ሕግጋቶች ብቻ እንዲተዳደር ሆነ። ይህ እሴት ግን በደንብ ማኅበረሰቡ ውስጥ አለ። በተለይም የገዳ ሥርዓት በሚተገበርባቸው አካባቢዎች ሕዝቡ በግልጽነት ችግሩን በመናገር መፍትሔ ሲያገኝ ነው የኖረው" ይላሉ አባገዳ ጎበና።

በሰላምና የአገር ጉዳዮች ላይ አባ ገዳዎች በባሕላዊ መንገድ እንዲሸመግሉ በተደረገባቸው አንዳንድ ቦታዎች ጥረታቸው ሳይሳካ የቀሩበት ሁኔታ እንዳለ አባገዳው ያስታውሳሉ።

እንደዚህ ዓይነቶች ችግር ሊከሰቱ የቻሉት ግን የሽምግልና እሴቱ ችግርን ለመፍታት ዋጋ ቢስ ሆኖ ሳይሆን፣ የሽምግልናን ዋጋ ወዳልተረዱት አካላት በሚላክበት ጊዜ የሚገጥም ነው ይላሉ።

"ኦሮሞ ሽምግልና የሚልከው ተስፋ ወደሚያደርግበት ቀዬ ነው፤ ዝም ብሎ በደመ ነፍስ አይሔድም። ሽምግልና የሚኬድባቸው አካላትም የሕዝቡን እሴት የተረዱ መሆን አለባቸው፤ የሽምግልናን ጥቅምና እሴት ወዳልተደረዱ ሰዎች ሽምግልና አይኬድም" ብለዋል።