'ልጅ እያሳደግሽ ኳስ መጫወት አትችይም ተብዬ ነበር'

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጄሲካ ማክዶናልድ እግር ኳስ ሜዳ ላይ ድል ሳይቀናት ሲቀር አሊያም ልምምድ ላይ ኳስ ስታበላሽ ምክንያቱ ልጇ ነበር።
ሰዎች እንደሚሏት ልጇ 'እያሰናከላት ነው'።
'ልጅ እያሳደግሽ ኳስ መጫወት አትችይም ተብዬ ነበር' ትላለች።
ሕፃናት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ቦት እንዳታስቀምጠው ኪሷ አይፈቀወድም። ያላት አማራጭ በጋሪ እየገፋች አምጥታ ከሜዳው አንዱ ጥግ ማስቀመጥ ነበር።
በፈረንጆቹ 2019 የአሜሪካ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫን ስታነሳ ልጇ አድጎ በደስታ ብልጭልጭ ወረቀት ሲበትን ታይቷል።
'ልጄ ለኔ አሰናካይ ሳይሆን ሕልሜን እንዳሳካ መነቃቃት የሚሆነኝ ነው። በየቀኑ እሱን ሳየው እነቃቃለሁ። እንሂድ፤ እናድርገው፤ ላንተ ስል ላድርገው እላለሁ' ትላለች ከቢቢሲ ስፖርት ጋር ቆይታ ያደረገችው ጄሲካ።
ጄሲካ በፈረንጆቹ 2012 ጄሬማያህን ስትገላገል ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ጨዋታና ልጅ ማሳደግ አብረው የሚሄዱ አልነበሩም።
በርካቶች አሁንም አብረው አይሄዱም ሲሉ ቢከራከሩም፤ ለውጦች ግን እየተስተዋሉ ነው።
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ የወሊድ እረፍትን በተለመከተ አዲስ ሕግ በዚህ ሳምንት ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲሱ ደንብ እግር ኳስ ተጫዋቾች የ14 ሳምንት የወሊድ እረፍት እንዲፈቀድላቸው ይወስናል ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህ ወቅት እግር ኳስ ተጫዋቾቹ ሙሉ ደመወዛቸው አሊያም ሁለት ሶስተኛው እንዲከፈላቸው ይላል።
ለጄሲካ ይህ መልካም ዜና ነው። በቤተሰብ ምክንያት በርካቶች ፕሮፌሽናል እግር ኳሰኝነታቸውን ሲተዉ ተመልክታለችና።
"ምንም እንኳ ቢዘገይም ቀስ በቀስ ወደፊት እየተጓዝን ነው" ባይ ናት የ32 ዓመቷ የዓለም ዋንጫ ባለድል።
በክለብ ደረጃ ለኖርዝ ካሮላይና ካሬጅ የምትጫወተው ጄሲካ 'ነብሰ ጡር በመሆኔ ብቻ ትችት ይደርስብኝ ነበር' ትላለች።
በወቅቱ 23 ዓመቷ ነበር። በጉዳት ምክንያት የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን አባል መሆን አልቻለችም በጊዜው።
የብሔራዊ ቡድን አምበል የሆነችው ክሪስቲ ፒርስ ብቻ ነበረች ልጅ እያላት እግር ኳስ የምትጫወተው። ይህ ደግሞ ለጄሲካ ማበረታቻ ሆናት።
አውስትራሊያ ሄዳ ለጥቂት ወራት ከተጫወተች በኋላ ወደ አሜሪካ ተመልሳ የሃገሪቱን የሴቶች ሊግ ተቀላቀለች።
ነገር ግን ከክለብ ክለብ ስትቀይር፤ ከግዛት ግዛት ስትዘዋወር አንድ ቦት ረግታ መቀመጥ አልቻለችም። ልጇም አብሯት ይንከራተት ነበር።
"ከቦታ ቦታ በጣም እዘዋወር ስለነበር አምኜ ልጄን የምተውበት ሥፍራ እንኳን አልነበረኝም። ያለኝ አማራጭ ልጄን ይዤ ወደ ሜዳ መሄድ ነበር።"
ጄሬማያህ እናቱ የዓለም ዋንጫን ስታነሳ ፈረንሳይ ነበር። አብሯት ሲቦርቅም ታይቷል።
የአይስላንድ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ የሆነችው ጉድዮርግ ጉናርስዶቲርም እግር ኳስ ተጫዋች ሆና ቤተሰብ እንዴት መመሥረት እንደምትችል ግራ ይገባት እንደነበር ትናገራለች።
እናት ለመሆን ያደረገችው ጉዞ በርካታ መከራ ይዞ የመጣ ነበር።
የቡድን አጋሮቿ ነብሰ ጡር በነበሩበት ጊዜ ያዩትን ስለምታውቅ የነበራት አማራጭ ሳትጎዳ ተጎድቻለሁ ብሎ ከሜዳ መራቅ ነበር። ነገር ግን ይህን ማድረግ አልመረጠችም።
"ወንድ እግር ኳስ ተጫዋቾችን ብትመለከች፤ ልጅ ሲወልዱ የቤተሰብ ሰው ተደርገው ነው የሚቆጠሩት እንጂ ሌላ ጣጣ የለባቸውም። ለሴቶች ግን አሉታዊ ተፅዕኖ ነው ያለው" ትላለች ጉድዮርግ።
"ምክንያቱም እኛ ልጅ ስንወልድ ከሜዳ እንርቃለን፤ ልጆቻችንን መንከባከብ አለብን፤ ክብደት ልንጨምር እንችላለን። ይሄን ሁሉ ተወጥተሽ ቶሎ ከተመለስሽ ደግሞ መልካም እናት እንዳልሆንሽ ትቆጠሪያለሽ።"
ጉድዮርግ መንታ ልጆች ከወለደች በኋላ ወደ ሜዳ ተመለሰች። ጡት ማጥባት ስለነበረብኝ እንጂ ከዚህም ፈጥኜ መመለስ አችል ነበር ትላለች።
የፊፋ መመሪያ
አዲሱ የፊፋ መመሪያ ክለቦች ከወሊድ የተመለሱ ተጫዋቾችን ወደ ቡድናቸው እንዲመልሱ ያስገድዳል። በቂ የሆነ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙም ያሳስባል።
መመሪያው፤ ክለቦች በወሊድ ምክንያት ተጫዋቾች ከሜዳ ከራቁ አዳዲስ ተጫዋቾችን ለአጭር ጊዜ ማስፈረም እንዲችሉ መስኮት ይሰጣል።
ልጅ የወለዱ እግር ኳስ ተጫዋቾች ልጆቻቸውን ጡት እንዲያጠቡ እንዲፈቅድላቸውም በመመሪያ ላይ ተመለክቷል።
ነገር ግን ለተጫዋቾች የሚፈቀደው ቢያንስ የ14 ሳምንታት የወሊድ እረፍት እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ያሉ ሃገራት የሚፈቅዱት እንደሚፈቅዱት 39 ሳምንታት ድረስ እንዲለጠጥ አይፈቀድም።
ምንም እንኳ ጄሲካና የሙያ አጋሮቿ አዲሱ መመሪያ ሁሉንም ያሟላ ነው ብለው ባያስቡም አንድ እርምጃ ወደፊት እንደሆነ አይክዱም።
ጄሲካ የዓለም ዋንጫ ስታነሳ ከብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ልጅ ያላት እሷ ብቻ ነበረች።
ጄሲካ በርካቶች እሷና ልጇ በዓለም ዋንጫ መድረክ ላይ በደስታ ሲቦርቁ የተመለከቱ ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች 'ዕድለኛ ነሽ' ሲሏት ስትሰማ ደስ እንደሚላት አትደብቅም።
"ተፅዕኖ እንደፈጠርኩ ሲሰማኝ እደሰታለሁ።"












