ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ወታደራዊ መኮንኖች ሴት ወታደሮች ላይ ወሲባዊ ጥቃት በማድረስ ተባረሩ
የአሜሪካ ጦር አስራ አራት ከፍተኛና ዝቅተኛ አመራር ያሉ ወታደራዊ መኮንኖች በሴት ወታደሮች ላይ ግድያን ጨምሮ ወሲባዊ ጥቃቶችና ትንኮሳን ፈፅመዋል በሚል አባሯቸዋል።
በቴክሳስ በሚገኘው የፎርት ሁድ የጦር ሰፈርም ነው እነዚህ ተደጋጋሚ ጥቃቶች የተፈፀሙት።
ቫኔሳ ጉሊየን የተባለች ወታደር በባለፈው አመት መገደሏንም ተከትሎ ነው በጦር ሰፈሩ ላይ ምርመራ የተጀመረው።
የ20 አመቷ ቫኔሳ ለሁለት ወር ያህል ጠፍታ የነበረ ሲሆን የአስከሬኗም የተወሰነ ክፍል የተገኘው በሰኔ ወር ነበር። በጦር ሰፈሩ ውስጥ በድብደባ እንደተገደለችም መርማሪዎች ገልፀዋል።
በሞቷ ዋነኛው ተጠርጣሪ የጦር መኮንኑ አሮን ሮቢንሰን ፖሊስ በቁጥጥር ስር ሊያውለው ሲል ሃምሌ ወር ላይ ራሱን አጥፍቷል።
የቫኔሳ ቤተሰቦች በአሮን ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባታል ቢሉም ባለስልጣናቱ በበኩላቸው ወሲባዊ ጥቃትና ትንኮሳ ሪፖርት አልደረሰንም በማለት ተናግረዋል። የቫኔሳ ግድያ የምርመራ ጉዳይ ገና አልተቋጨም።
የጦሩ ዋና ፀሃፊ ራያን ማካርቲ እንዳሉት " በፎርት ሁድ ጦር ሰፈር የተፈፀሙት ጉዳዮች ቀጥታ አመራሩ ጉድለት ጋር የተያያዙ ናቸው"
ከዚህም በተጨማሪ በጦር ሰፈሩ ጠፉ የተባሉ ወታደሮችንም በተመለከተ አዲስ ፖሊሲ እንዲወጣ ጦሩ ትእዛዝ አስተላልፏል።
የተባረሩትና የታገዱት ወታደራዊ መኮንኖች ጉዳይ የተገለፀው በትናንትናው ዕለት ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ሜጀር ጄኔራሎቹ ስኮት ኤፍላንድትና ጄፈሪ ብሮድዋተር ይገኙበታል።
በተለይም የቫኔሳ ግድያ "ሁላችንም አስደንግጦናል። በአሜሪካ ጦርም ውስጥም ሆነ በፎርት ሁድ ጦር ውስጥ ስር የሰደደውን ችግር እንድንመለከተው አድርጎናል" ብለዋል ዋናው ፀሃፊው።
አክለውም "በስርዓታችን፣ በፖሊሲዎቻችንና ራሳችንንም በጥልቀት እንድንመለከትና እንድንፈትሽም አስገድዶናልም" በማለት ለሪፖርተሮች ተናግረዋል።
በፎርት ሁድ በሚገኘው የጦር ሰፈር በአንድ አመት ብቻ 25 ወታደሮች በተለያዩ ምክንያቶች ሞተዋል። አንዳንዶቹ ራሳቸውን አጥፍተዋል፣ ተገድለዋል ወይም አደጋ ደርሶባቸው ነው የሞቱት በማለት አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።