ሚሊዮን ዶላሮች የሚያስታቅፈው የደቡብ አፍሪካ ሎቶሪ ተጭበርብሯል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የደቡብ አፍሪካ ሎቶሪ 5-6-7-8-9-10 ተከታታይ ቁጥር ሆኖ መውጣቱ እያነጋገረ ነው
የደቡብ አፍሪካ ሎቶሪ የአሸናፊው ቁጥር አስገራሚ ሆኖ ወጥቷል፡፡ ከ5 ጀምሮ እስከ 10 ቁጥሮች በተርታ መውጣታቸው አገሬውን ጉድ አሰኝቷል፡፡
ቁጥሮቹ ተከታታይ መሆናቸው ብቻ አይደለም ግርታን የፈጠረው፡፡ በአንድ ጊዜ የናጠጠ ሚሊዮነር የሚያደርገው አንደኛ እጣ ያሸነፈው ሰው አንድ ሰው አለመሆኑ ነው፡፡
20 ሰዎች አሸናፊ ነን ብለው መቅረባቸው ሌላ ጥርጣሬን ፈጥሯል፡፡ እንዴት 20 ሰዎች ይህንን ተከታታይ ቁጥር ሊገምቱ ይችላሉ ነው ተጭበርብሯል የሚል ጥርጣሬን የፈጠረው፡፡
የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ሎቶሪ እጣውን ያወጣሁት በሕዝብ ፊት በቴሌቪዥን በቀጥታ ሥርጭት ነው፣ ይህ የዕድል ጉዳይ ነው ቢሉም ፖሊስ ግን ነገሩን ስላላማረው ምርመራ እጀምራለሁ ብሏል፡፡
አንድን የአሸናፊ ቁጥር 20 ሰዎች ማግኘታቸው በፍጹም ያልተመለደና የመከሰት ዕድም በጣም አነስተኛ የሚባል ነው፡፡ በዚያ ላይ የአሸናፊ ቁጥር ከ5 ጀምሮ ተከታታይ አሀዝ መያዙ አጋጣሚ ብቻ ተብሎ የሚታለፍ አልሆነም፡፡
ብሔራዊ ሎቶሪው እንደሚለው 20 ሰዎች ቁጥሩን በትክክል በመገመታቸው እያንዳንዳቸው 370 ሚሊዮን ዶላር ይሰጣቸዋል፡፡
አንድ ሰው የደቡብ አፍሪካ ‹ፓወርቦል› ሎተሪን የማሸነፍ ዕድሉ ከ42 ሚሊዮን 375ሺ 200 ሰዎች መካከል 1 ብቻ ነው፡፡
የሎቶሪ አስተዳደሩ በትዊተር ሰሌዳው ላይ ‹‹እንኳን ደስ ያላችሁ፤ 20 አሸናፊዎች የቁጥሮቹን ቅደም ተከተል በትክክል ስለገመታችሁ ደስ ይበላችሁ!›› ሲል የደስታ መግለጫ አስተላልፏል፡፡
ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት የወጣው ሎቶሪ ቁጥርና የአሸናፊዎች ብዛት ግራ የተጋባው አገሬው በማኅበራዊ የትስስር ገፆች በመውጣት ቧልትና ፌዝ ሲጋራ አምሽቷል፡፡












