ሕንድ የቻይና መተግበሪያዎችን ማገዷን ቀጥላለች

አሊ ኤክስፕረስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ሕንድ በቻይና መተግበሪያዎች ላይ የምትጥለው ዕገዳ ቀጥሎ ቀጣዩ ባለዕጣ የኤሌክትሮኒክስ መገበያያው አሊኤክስፕረስ ሆኗል።

የሕንድ መንግሥት የሳይበር ደኅንነት ስጋቶችን ምክንያት በማድረግ ተጨማሪ 43 ቻይና መተግበሪያዎችን ያገደ ሲሆን አጠቃላይ ቁጥሩን ወደ 220 ከፍ አድርጎታል።

የሕንድ እገዳ የቀጠለው ባለፈው ሰኔ በሁለቱ አገራት መካከል በተካሄደ ውጊያ 20 የሕንድ ወታደሮች ከተገደሉ በኋላ ውጥረቱን ለማቃለል አገራቱ ውይይት በሚያደርጉበት ወቅት ነው።

መተግበሪያዎቹ የሕንድን "ሉዓላዊነት እና ታማኝነት" በሚጎዱ ተግባራት ላይ ተሰማርተዋል ሲል የሕንድ መንግሥት ይገልጻል።

የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋቶችን "ተደጋግመው መነሳታቸውን" እንደ "ሰበብ" ገልፀው "ፍትሐዊ፣ ገለልተኛ እና አድሎአዊ ያልሆነ የንግድ ትስስር" እንደሚኖር ተስፋቸውን ገልጸዋል።

ዕገዳዎቹ የመረጃ ወይም የግላዊነት ደኅንነት ስጋቶችን መሠረት ያደረጉ ሳይሆን ለቻይና የተሰጡ ምላሾች እንደሆኑ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።

የቴክኖሎጂ ጸሐፊው ፕራሳንቶ ኬ ሮይ እንደሚሉት "ኒው ዴልሂ ከቻይና ጋር ግንኙነት ያላቸውን መተግበሪያዎች በማገድ ለቻይና መልዕክት ለማስተላለፍ መሆኑ ግልፅ ነው" ይላሉ።

አክለውም "ለዓመታት የግላዊ መረጃ የደኅንነት ስጋቶች የቻይናን ጨምሮ ለሌሎች መተግበሪያዎች ቢኖሩም እ.አ.አ ከሰኔ 2020 በፊት ምንም ዕገዳ አልተደረገም።"

የኑክሌር መሣሪያ የታጠቁት ጎረቤታሞች ከለፈው ዓመት ሚያዝያ ጀምሮ ወታደሮቻቸውን በድንበር ላይ አሰማርተዋል። በሰኔ ወር በአጨቃጫቂው የሂማልያ ድንበር ላዳህ በሚገኘው የጋልዋን ሸለቆ የተነሳው ፍጥጫ ግን ሁኔታው አባብሷል።

አንድም ጥይት ሳይተኮስ ሃያ የሕንድ ወታደሮች ህይወት አልፏል። ሕንድ በሁለቱም ወገኖች ላይ ጉዳት ደርሷል ስትል ቻይና በበኩሏ ሟቾችን ወይም የቆሰሉትን ወታደሮች ቁጥር አላረጋገጠችም።

አገራቱ ውይይቶችን ጀምረው ግጭት ውስጥ ላለመግባት ቢስማሙም ጠላትነትን የሚጨምሩ ንግግሮች ተደምጠዋል። ዕገዳዎቹ ቀጣይ ውይይቶችን እንዴት እንደሚነኩ እስካሁን ግልፅ አልሆነም።

እንደ ሮይ ያሉ ባለሙያዎች ሌሎች አሳሳቢ ጉዳዮችም አሉ ይላሉ።

"ላለፉት ሁለት ዓመታት የተማሪዎችን ተቃውሞንም ሆነ የመተግበሪያ ዕገዳን አስመልክቶ 'ብሔራዊ ደኅንነት እና በሉዓላዊነት ላይ ስጋት ላይ ወድቋል' መባሉ ነው።"

በተለይም ከሦስት ዓመታት በፊት ግላዊነትን እንደ መሠረታዊ መብት አጽንቶ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ከተሰጠም በኋላ በሕንድ ያለው የግላዊ ደኅንነት ሕጎች አለመኖርም "እንዲሁ አሳሳቢ ነው" ብለዋል።

"የሕንድና የአሜሪካን ጨምሮ በጣም ብዙ መተግበሪያዎች ከሚያስፈልጋቸው በላይ ተጨማሪ ግላዊ መረጃዎችን እና ፈቃዶችን ይሰበስባሉ" ሲሉ ያክላሉ።

"የተሻለው አማራጭ ቸግር ፈጣሪዎችን ለይቶ ችግራቸውን በመግለጽ ለተወሰነ ጊዜ የሚቆይ ዕገዳ መጣል ነው። ድርጅቶች ከግላዊ መረጃ ጋር የተጣጣሙ ሪፖርቶችን እንዲያቀርቡ መፍቀድ ነው" ብለዋል።