የዲሞክራቲክ ኮንጎ ሚሊሻ መሪ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞ የዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኦፍ ኮንጎ ሚሊሻ መሪ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት።
የሃገሪቱ ፍርድ ቤት ንታቦ ንታቤሪን በግድያ፣ በአስገድዶ መድፈር፣ ሴቶችን በኃይል ይዞ ማቆየት እና ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትን መመልመል በሚሉ ክሶች ጥፋተኛ ብሎታል።
ፍርድ ቤቱ የቀድሞውን የሚሊሻ መሪ ጉዳይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሲመለከት የቆየ ሲሆን፤ 178 ተጎጂዎችም ፍርድ ቤት ተገኝተው ምስክርነታቸው ሰጥተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂዩማን ራይትስ ዎች የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በበጎ ተቀብለውታል።
ሼክ በሚል መጠሪያ ስሙ የሚታወቀው ንታቦ ንታቤሪን፤ በምስራቅ ዲሞክራቲክ ኮንጎ የሚንቀሳቀሰው እና ናዱማ የኮንጎ መከላከያ ኃይል የተባለውን የሚሊሻ ቡድን ከሚመሩት መካከል አንዱ ነው።
በተፈጥሮ ማዕድናት በበለጸገው ምስራቃዊ የሃገሪቱ ክፍል ተደጋጋሚ የሆነ ግጭት ይከሰታል።
እአአ ከ1998 እስከ 2003 የዘለቀ የእርስ በእርስ ጦርነት በኮንጎ ተከስቶ የነበረ ሲሆን፤ ከእርስ በእርሱ ጦርነት በኋላም በርካታ ታጣቂ ኃይሎች ነፈጥ አንግበው ጥቃቶችን ማድረሳቸውን ቀጥለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ኃይል በምስራቅ ኮንጎ ሰላም ለማረጋገጥ ከፍተኛ ፈተና እየገጠመው ይገኛል።
የኮንጎ መንግሥት እአአ 2011 ላይ ነበር ንታቦ ንታቤሪ በንጹሃን ላይ ጥቃት አድርሷል በሚል የእስር ትዕዛዝ ያወጣበት።
መንግሥት ንታቦ ንታቤሪ የሚመራው ታጣቂ ቡድን ከሌሎች የሚሊሻ ቡድን ጋር በመሆን 400 ሰዎችን አስገድደው ደፍረዋል ከ300 የማያንሱ ሰዎችን ደግሞ ገድለዋል ይላሉ።
ለበርካታ ዓመታት ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተሸሽጎ የቆየው ንታቦ ንታቤሪን እአአ በ2017 ነበር በኮንጎ ተሰማርቶ ለሚገኘው የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል እጁን የሰጠው።












