ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ታሊባን፡ የአፍጋኒስታን መንግሥት ትምህርት ቤት ላይ በፈፀመው የአየር ጥቃት ሕጻናት ሞቱ
በአፍጋኒስታን ሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ታክሃር አውራጃ በሃይማኖታዊ ትምህርት ቤት ላይ በተፈፀመ የአየር ጥቃት 12 ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ገለፁ።
የአካባቢው ባለስልጣናት በእስላማዊ ትምህርት ቤት ላይ በደረሰው የአየር ጥቃት 11 ሕጻናት እና አንድ መምህር ተገድለዋል ሲሉ ተናግረዋል።
የአፍጋን መንግሥት በበኩሉ በጥቃቱ የተገደሉት የአፍጋን ወታደሮች ናቸው ሲል አስተባብሏል።
የአየር ጥቃቱ የተፈፀመው ታሊባን በፈፀመው የሽምቅ ጥቃት 30 ያህል የመንግሥት ወታደሮች ከተገደሉ በኋላ ነው።
ረብዑ ዕለት በደረሰው የአየር ጥቃት ተጨማሪ 14 ሰዎች ጉዳት አጋጥሟቸዋል ተብሏል።
ከተጎዱት መካከል ከትምህርት ቤቱ አጠገብ የሚገኝ መስጂድ ኢማም የሆኑት ግለሰብ፣ አብዱል አወል፣ መሆናቸውና ሆስፒታል መግባታቸውን ለቢቢሲ የአካባቢው ባለስልጣናት ጨምረው ተናግረዋል።
ጥቃቱ በተፈፀመበት ወቅትም በመስጂዱ እርሳቸውና ሕጻናቱ ብቻ እንደነበሩ አክለው ተናግረዋል።
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በአፍጋን መንግሥትና በታሊባን ወታደሮች መካከል ያለው ግጭት እየተካረረ የመጣ ሲሆን፣ ጀምረውት የነበረውን የሰላም ድርድር አጣብቂኝ ውስጥ ጥሎታል።
የአየር ጥቃቱ በተፈፀመበት አካባቢ የሚገኝ ሆስፒታል ተጎድተው የመጡት አብዛኛዎቹ ሕጻናት መሆናቸውን ተናግሯል።
የአፍጋን መንግሥት ግን መረጃው ሐሰት ነው ሲል ያስተባበለ ሲሆን፣ ነገር ግን በንጹሐን ላይ ጥቃት ተፈጽሟል የሚለውን ውንጀላ የሚያጣራ ቡድን መቋቋሙን ገልጿል።
በቅርብ ሳምንታት ውስጥ የታሊባን አማፂያንና የአፍጋኒስታን መንግሥት መካከል ባለው ግጭት የተነሳ 40 ሺህ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቀለዋል።
በዚህ ዓመት ብቻ 220 ሺህ አፍጋኒስታናውያን ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ስደተኞች ድርጅት አስታውቋል። ይህም ከፈረንጆቹ 2012 ጀምሮ የተፈናቀሉ ሰዎችን ቁጥር 4.1 ሚሊዮን አድርሶታል።