በዴሞክራቲክ ኮንጎ ከ1300 በላይ ታራሚዎች አመለጡ

እሰረኞች ያመለጡበት ማረሚያ ቤት

የፎቶው ባለመብት, RADIO OKAPI

ታትሟል

በምስራቃዊ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ በምትገኘው ቤኒ ከተማ ባለ አንድ እስር ቤት ላይ የእስላማዊ አማጽያን ቡድን በፈጸመው ጥቃት ከ1300 በላይ እሰረኞች ማምለጣቻውን የአከባቢው ባለስልጣናት ተናገሩ።

የተከማዋ ከንቲባ "አላይድ ዲፌንስ ፎርስ' ወይም 'ኤዲኤፍ' በሚል ስያሜ የሚታወቀው እስላማዊ አማጽያን ቡድን በማረሚያ ቤት ውስጥ የነበሩ አባላቱን ለማስለቀቅ በማሰብ ነው በማረሚያ ቤቱ ላይ ጥቃት የፈጸመው ብለዋል።

ካንግባዪ በሚባለው ማረሚያ ቤት ውስጥ ከነበሩት ታራሚዎች አብዛኛዎቹ ጥቃቱን ተከትሎ ያመለጡ ሲሆን 100 የሚሆኑ ታራሚዎች ግን እዛው ከክፍላቸው ሳይንቀሳቀሱ ጠብቀዋል።

ኤዲኤፍ በእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ ይደርሳል የሚለውን አድለዎ እና መገለል ለመዋጋት ከ20 ዓመታት በፊት በጎረቤት አገር ኡጋንዳ ነበር የተመሰረተው።

ቡድኑም በኡጋንዳ መከላከያ ኃይል በደረሰበት ተደጋጋሚ ጥቃት ምክንያት ዋነኛ መቀመጫውን ከኡጋንዳ ወደ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ምስራቃዊ ክፍል በማዘዋወር ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።

ነገር ግን ቡድኑ ይህንን ጥቃት ስለመፈጸሙ ምንም ያለው ነገር የለም።

የቤኒ ከንቲባ ሞደስቴ ባክዋናማሀ ለሬውተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ጥቃት ፈጻሚዎቹ በርካታ ቁጥር የነበራቸው ሲሆን የማረሚያ ቤቱን በሮች ለመስበርም የኤልክትሪክ መሳሪያ ተጠቅመዋል።

''ጥቃቱን የፈጸመው ኤዲኤፍ እንደሆነ እናምናለን'' ሲሉም ተደምጠዋል ከንቲባው።

ፖሊስ በበኩሉ ጥቃቱን ተከትሎ ካመለጡት ታራሚዎች መካከል 14 ታራሚዎችን አድኖ መያዙን የገለጸ ሲሆን ሁለት ታራሚዎች ደግሞ ከእስር ቤት ለማምለጥ በሞከሩበት ወቅት ከፖሊስ በተተኮባቸው ጥይት ሕይወታቸው ማለፉን በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው 'ኦካፒ' የሬድዮ ጣብያ ዘግቧል።

የዲሞክራቲክ ኮንጎ ጦር ቃል አቀባይ አንቶኒ ማሉሻይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከእስር ቤት ያመለጡትን ታራሚዎች ፈልጎ የመያዝ ስራው እንደቀጠለ ነው።

እአአ 2017 ላይ የኤዲኤፍ ተዋጊዎች ከዚሁ ማረሚያ ቤት አምልጠው ነበር።

በተፈጥሮ የማዕድን ሃብት በበለጸገው ምስራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኦፍ ኮንጎ ከሚንቀሳቀሱ በርካታ ታጣቂ ቡድኖች መካከል አንዱ ኤዲኤፍ ነው። የአገሪቱ መንግሥት እና የተባበሩት መንግሥታት በስፍራው ሰላም ለማስፈን ብዙ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።