ብራዚል ቻይና ሰራሽ የኮቪድ ክትባትን ለሕዝቧ ልታድል ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በዓለም ላይ ኮቪድ ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰባቸው አገራት ተርታ የምትመደው የደቡብ አሜሪካዋ ትልቅ አገር ብራዚል ቻይና ሰራሽ ክትባት ለሕዝቤ አድላለሁ ብላለች።
የሳኦ ፖሎ ገዥ ጃዎ ዶሪያ እንዳሉት የፌዴራል መንግሥት 46 ሚሊዮን ጠብታዎችን ለመግዛት ስምምነት ላይ ደርሷል። የክትባቱ ስም ኮሮናቫክ ነው። የተመረተው ደግሞ ሲኖቫክ በሚባል የቻይና ኩባንያ ነው።
የክትባት ዘመቻው መቼ ይጀመራል በሚል የተጠየቁት የሳኦ ፖሎ ገዥ በፈረንጆች አዲሱ ዓመት የመጀመርያ ወር ላይ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ብራዚል ከ5 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሕዝቧ በዚሁ ተህዋሲ ተጠቅቷል። በዓለም ላይ በተህዋሲ የተያዘባቸው ዜጎች ብዛት ከአሜሪካና ሕንድ ቀጥሎ ሦስተኛዋ ተጎጂ አገር ናት።
ተህዋሲው ባደረሰው ሞት ቁጥር ደግሞ ሕንድን በልጣ ከአሜሪካ ተከትላ በ2ኛነት ላይ ትቀመጣለች። 155ሺ ዜጎቿ ከተህዋሲው ጋር በተያያዘ ሞተውባታል።
የኮሮናቫክ እደላው የሚጀምረው የብራዚል የጤና ሚኒስቴር የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ሲያጸድቀው ብቻ ነው። ለጊዜው ይህ አልሆነም። ኮሮናቫክ በቻይናው ሲኖቫክ የመድኃኒት ኩባንያ የተመረተ ሲሆን ተስፋ ከተጣለባቸው ክትባቶች አንዱ ነው።
ብራዚል ከዚህ ቻይና ሰራሽ ክትባት ሌላ በእንግሊዙ የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲና በግዙፉ መድኃኒት አምራች አስትራዜኔካ ጥምረት እየተሞከረ ያለውንና ዓለም ትልቅ ተስፋ የጣለበትን ክትባትም ገዝታ ለሕዝቧ ታድላለች።
የሳኦ ፖሎ ገዥ ኮሮናቫክ በግዛቲቱ የምርምር ማዕከል ውስጥ ቡታንታን ኢንስቲትዩት ውስጥ የመጨረሻ ሙከራዎች እየተደረጉበት ነው ብለዋል። ቡታንታን ኢንስቲትዩት ከትናንት በስቲያ ሰኞ የቻይናው ኮሮናቫክ ክትባት አስተማማኝ እንደሆነ ተናግሮ ነበር።
''በመጨረሻ ምዕራፍ አንዳንድ ሙከራዎች ውጤታማ እንደሆነ ተመልክተናል'' ብሏል ኢንስቲትዩቱ። ሆኖም በክትባቱ ዙርያ የሚቀሩ የመጨረሻ የማጣሪያ ሙከራዎች እንዳሉ ኢንስቲትዩቱ አልካደም።
ሲኖቫክ ያመረተው ኮሮናቫክ መቶ በመቶ ፍቱን ነው የሚለውን ለመናገር የመጨረሻ ምርመራ ውጤቶች እየተጠበቁ ነው። ኮሮናቫክ ባለሁለት ጠብታ ክትባት ነው።
የክትባት ዘመቻውን ለመጀመር የመጨረሸ ዝግጅቶችም ጎን ለጎን እየተደረጉለት ነው። ሲኖቫክ ያመረተው የኮሮናቫክ ጠብታ ሙከራዎች ከብራዚል ሌላ በቱርክና በኢንዶኒዚያም እየተካሄዱ ነው።












