ሜክሲኮ፡ በኮሮና የሞቱት ከንቲባ ባለቤት በቦታቸው እንድታገለግል ተመረጠች

የፎቶው ባለመብት, Luis Alberto Díaz
በሜክሲኮ የአንዲት ግዛት ከንቲባ በኮሮናቫይረስ መሞታቸውን ተከትሎ የአርባ አመት ባለቤታቸው በከንቲባነት እንድታገለግል መመረጧን ከሰሞኑ ተዘግቧል።
ፒየር አንግሊ ካማቾም እስከ መጪው ምርጫ ድረስ በባለቤታቸው ስፍራ ከንቲባ ሆነው ያገለግላሉ ተብሏል።
የሲናሎዋ ግዛት ምክር ቤት ፒየር አንግሊ ካማቾን በከፍተኛ ድምፅ ድጋፍና በአንድ ድምፀ ተአቅቦ መሾሙን አስታውቋል።
የ46 አመት ባለቤቷ ከንቲባ ካርሎ ማሪዮ ኦርቲዝ በልጅነታቸው ወቅት የኩላሊት ንቅለ ተከላ ቀዶ ጥገና አድርገው የነበረ ሲሆን ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ ናቸው ከተባሉትም ወገን ነበሩ።
ባለፈው ሳምንትም በኮሮናቫይረስ ህይወታቸው አልፏል።
ካርሎ ማሪዮ ህይወታቸው ከማለፉ በፊት ለሁለተኛ ጊዜ ተመርጠው በሲናሎዋ አስተዳደር ሳልቫዶር አልቫራዶ የምትባለውንም ግዛት በከንቲባነት ሲያገለግሉ ነበር።
ከሁለት አመት በፊት በተደረገ የህዝብ ቆጠራም የግዛቲቷ ነዋሪ 80 ሺህ ያህል ነው።
በሞቱት ባለቤታቸው ስፍራ የተተኩት ፒየር አንግሊ ካማቾ በሜክሲኮ መንግሥት የማህበራዊ ደህንነት ተቋም ውስጥ ነው የሚሰሩት።
ምርጫ ይካሄድበታል ተብሎ እቅድ ከተያዘለትም እስከ ሚቀጥለው ወር ድረስም በከንቲባነት ታገለግላለች።
የቀድሞ ባለቤቷንም ስፍራ ይዛ ለማገልገል በመመረጧ ክብር እንደሚሰማትም ገልፃለች።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ ከተጠቁት መካከል አንዷ በሆነችው ሜክሲኮ፤ ወረርሽኙ ከተከሰተ ጀምሮ በሜክሲኮ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 847 ሺህ ያህል ሲሆን ከነዚህም መካከከል 86 ሺህ 59 ሰዎች ሞተዋል።













