ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሴቶች መብት፡ በናይጄሪያ 9 ሴቶችን የገደለው ግለሰብ ሞት ተፈረደበት
በናይጄሪያ ደቡባዊ ከተማ ፖርት ሃርኮርት 9 ሴቶችን የገደለው ግለሰብ የሞት ፍርድ ተወሰነበት።
ድርጊቱ በናይጄሪያ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር።
አቃቤ ሕግ እንዳለው የ26 ዓመቱ ግለሰብ ግራሺየስ ዴቪድ ዌስት፤ እአአ. ከሐምሌ ወር እስከ መስከረም 2019 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው በሆቴል ክፍሉ ውስጥ ሴቶቹን አንቆ የገደላቸው።
ግድያውን የፈፀመው በተከታታይ ሲሆን፤ ሴቶቹን እጅና እግራቸውን በአንሶላ አስሮ ከመግደሉ በፊት ወሲብ እንደፈፀመባቸውም ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
አንቆ ለመግደልም አንሶላ መጠቀሙን ፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
አብዛኞቹ ሟቾች በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ ሴቶች መሆናቸው ተነግሯል።
ግለሰቡ ይህንን ወንጀል ለመፈፀም ርካሽ የሆኑ ሆቴሎችን ይጠቀም እንደነበርና ሆቴሎቹም የደህንነት ካሜራ እንዳልነበራቸው እንዲሁም ደህንነታቸውም የተጠበቀ እንዳልነበር ፖሊስ ገልጿል።
ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ አዶልፕስ ኢኔቤሊ፤ ግለሰቡ በስቅላት መቀጣት አለበት ብለዋል።
የሞት ፍርድ በናይጀሪያ የተለመደ አይደለም። ለመጨረሻ ጊዜ የተላለፉ 3 የሞት ፍርዶች የተፈፀሙት በ2016 ነበር።
ፖሊስ አክሎም ግለሰቡ ሌላ ቦታ ሌሎች ስድስት ሴቶችን እንደገደለ ቢያምንም፤ መረጃ ባለመገኘቱ ምክንያት በእነዚህ ግድያዎች ክስ ሳይቀርብበት ቀርቷል።
አንዲት ሴት ከግድያው ያመለጠች ቢሆንም በፍርድ ሂደቱ ግን ለምስክርነት እንዳልቀረበች ተዘግቧል።
ግለሰቧ ምንም እንኳን ግዛቱን ለቅቃ እንዳልወጣች ቢነገርም ያለችበት የት እንደሆነ እንደማይታወቅ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ወንጀለኛው ማን ነው?
ዴቪድ ዌስት ቡጉማ በተባለችውና በአሳ ሃብቷ እንዲሁም ነዳጅ አምራች በሆነችው የባህር ዳርቻ ከተማ ነው የተወለደው።
ከተማዋ እአአ. በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ በናይጄሪያ ኒጀር ዴልታ ውስጥ የማንግሮቭ ረግረጋማ ቦታዎች ዘመቻ ከሚያካሂዱ የነዳጅ ታጣቂዎች ጋር የተያያዘ ታሪክ አላት። ታጣቂዎቹ ከነዳጅ ተጠቃሚነት ጋር የተያያዘ ጥያቄ ያነሱ ነበር።
ፖሊስ እንዳለው ዴቪድ ዌስት 'ደይ ግባም' በመባል የሚታወቁት የማፊያ ቡድን አባል ነበር። እነዚህ የማፊያ ቡድን የወጡት ደግሞ ከታጣቂ ቡድኑ እንደሆነ ይነገራል።
ወንጀለኛውን የሚያውቁት ሰዎችም ከአንድ በላይ ጋብቻ ባለበት ቤተሰብ ብቸኛ ልጅ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል። እናቱ እና እርሱ ከሌሎቹ ቤተሰቦቹ ተነጥለው ለብቻቸው ነበር የሚኖሩት።
ፍርድ ቤት ላይ ግለሰቡን የተመለከቱ ጋዜጠኞችም የግለሰቡ ባህሪ የማይጨበጥ እንደነበር ተናግረዋል።
ችሎቱን የተከታተለው አንድ ጋዜጠኛም የግለሰቡን ሁኔታ " ቶሎ ይቆጣል ፣ በዳኛው መሃል ጣልቃ ይገባ ነበር፣ ጠበቃ ቢኖረውም ራሱን ለመከላከል ይሞክር ነበር" ሲል ገልጾታል።