ሲንጋፖር የዜጎቿ ፊት አይቶ ማንነታቸውን የሚለይ መሣሪያ መተግበር ጀመረች

ሲንጋፖር የዜጎቿ ፊት አይቶ ማንነታቸውን የሚለይ መሣሪያ (ፌሻል ሪኮግኒሽን) በመተግበር በዓለም ቀዳሚዋ አገር ሆናለች።
መሣሪያው ለግል እና መንግሥታዊ አገልግሎቶች ለማግኘትም ጥቅም ላይ ይውላል።
የአገሪቱ የቴክኖሎጂ ኤጀንሲ መሣሪያው የዲጂታል ምጣኔ ሀብት መሠረት ነው ብሏል።
የአንድን ግለሰብ ማንነት ከፎቶ ወይም ከቪድዮ የሚለየው ይህ መሣሪያ እውነተኛ ሰውን ከሐሰተኛ ምስል ወይም ከተቀናበረ ተንቀሳቃሽ ምስል ይለያል።
መሣሪያውን ለሲንጋፖር ያቀረበው የዩናይትድ ኪንግደም ድርጅት መስራች አንድሪው በድ “አንድ ሰው የእውን መኖሩን ያረጋግጣል። ፎቶ፣ ቪድዮ ወይም የተቀናበረ ምስል (ዲፕፌክ) መለየት ይችላል” ሲሉ አስረድተዋል።
መሣሪያው ከባንክ እና ከአገር አቀፍ መታወቂያ ሰጪዎች ጋር የተሳሰረ ነው። ዜጎች የመንግሥት ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶች እንዲያገኙም ያስችላል።
መሣሪያው እንዴት ጥቅም ላይ ይውላል?
የሰዎችን ፊት በማየት ማንነታቸውን የመለየት ሂደት ሁለት አይነት ነው። በእንግሊዘኛው ፌሻል ሪኮግኒሽን [የሰዎችን ፊት በማየት መለየት] እና ፌሻል ቬሪፊኬሽን [የሰዎችን ፊት በማየት ማንነትን ማረጋገጥ] ይባላሉ።
የአንድን ሰው ምስል ወይም ቪድዮ ወስዶ ቀደም ሲል ከተከማቸ ምስል ወይም ቪድዮ ጋር በማነጻጸር ማንነቱን ወይም ማንነቷን መለየት ይቻላል።
ፌሻል ቬሪፊኬሽን ከፌሻል ሪኮግኒሽን የሚለው መሣሪያው ጥቅም ላይ ሲውል የዜጎች ፍቃድ አስፈላጊ በመሆኑ ነው። ወደ ሰዎች ባንክ ወይም ተንቀሳቃሽ ስልክ መግባትም ይቻላል።
በሌላ በኩል ፌሻል ሪኮግኒሽን በባቡር ጣቢያ ወይም ሌሎች አካባቢዎች ይሠራል። ለምሳሌ በወንጀል የሚፈለግ ሰው እየተጓጓዘ ቢሆን ጥቆማ ይሰጣል።
ቴክኖሎጂውን በአገሪቱ የተገበሩት አንድሪው “ፌሻል ሪኮግኒሽን ማኅበራዊ ተጽዕኖ አለው። ፌሻል ቬሪፊኬሽን ግን ጉዳት አልባ ነው” ይላሉ።
ሆኖም ግን የግል መረጃ ደህንነት ተሟጋቾች ያለ ግለሰቦች ፍቃድ ስሱ መረጃ ሊወሰድ ይችላል ብለው ይሰጋሉ።
“ተቆጣጣሪና በቁጥጥር ሥር ያሉ ሰዎች ሲኖሩ ፍቃድ መስጠት የሚለው ቃል ትርጉም አይኖረውም። የኃይል አለመመጣጠን አለ” የሚሉት የሕግ ባለሙያና የግል መረጃ ጥበቃ ባለሙያ ሎአንስ ኮቫክስ ናቸው።
ለነጋዴ ወይስ ለመንግሥት?
የአሜሪካ እና የቻይና የቴክኖሎጂ ተቋሞች መሣሪያውን ይጠቀማሉ።
ለምሳሌ የባንክ መተግበሪያዎች መሣሪያውን ከሚያበረታቱ መካከል ይጠቀሳሉ። አፕል ‘አፕል ፌስ አይዲ’፣ ጉግል ደግሞ ‘ፌስ አንሎክ’ የተባሉ አሠራሮችን ዘርግተዋል።
የቻይናው አሊባባም ተመሣሣይ መተግበሪያ አለው።
ፌሻል ቬሪፊኬሽን የሚጠቀሙ መንግሥታት አሉ። እንደ ሲንጋፖር ከብሔራዊ መታወቂያ ጋር ለማጣመር ያሰቡ ግን ጥቂት ናቸው።
አሜሪካ ውስጥ መንጃ ፍቃድ እንደ መታወቂያ ስለሚያገለግል መሣሪያውን ከብሔራዊ መታወቂያ ጋር ማገናኘት የሚለውን ሐሳብ ለመተግበር ያስቸግራል።
ቻይና ፌሻል ቬሪፊኬሽንን ከብሔራዊ መታወቂያ ጋር ለማጣመር አልሞከረችም።
ዜጎቿ አዲስ ስልክ ሲገዙ የፊት ምስላቸው ተወስዶ ከብሔራዊ መታወቂያ ጋር እንዲነጻጸር የሚያዝ ሕግ አምና ወጥቷል።
አውሮፕላን ማረፊያዎች እና የተለያዩ አገሮች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም መሣሪያውን ይጠቀማሉ።
የሲንጋፖር ጅማሮ
ሲንጋፖር ውስጥ መሣሪያው በግብር ቢሮ፣ በባንክና ሌሎችም ተቋሞች ጥቅም ላይ እየዋለ ነው።
በወደብ አካባቢ እንዲሁም ተማሪዎች ፈተና መውሰዳቸውን ለማረጋገጥም ይውላል። ነጋዴዎችም የመንግሥት መስፈት አሟልተው መጠቀም ይችላሉ።
የሲንጋፖር ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ኃላፊ ክዎክ ኬውክ ሲን እንዳሉት፤ መሣሪያውን ለመጠቀም የዜጎች ይሁንታ ያስፈልጋል።
ይሁንታ ያገኘ ማንኛውም አካል መሣሪያውን መተግበር እንደሚችልም ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂው ንግድ እንደሚያጧጧፍ ተስፋ ያደርጋሉ።
በተጨማሪም መሣሪያውን የሚጠቀሙ ተቋሞች የግለሰቦችን መረጃ ስለማያከማቹ የግል መረጃ ደህንነት እንደሚጠበቅ ኃላፊው ይናገራሉ።












