የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በቂ ሴቶች ባለመኖራቸው ፓርላማው እንዲበተን ፕሬዚዳንቱን ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, AFP Contributor
በኬንያ ውስጥ ያለው የሴቶች ፓርላማ አባላት ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ፓርላማው እንዲበተን የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዳኛ ዴቪድ ማራጋ ጠይቀዋል።
ዳኛው ጥያቄያቸውን ያቀረቡት ለፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በተፃፈ ደብዳቤ ነው።
የሴቶች የፓርላማ አባላት ቁጥር አነስተኛ መሆን ህገ መንግሥቱን የጣሰ ነው እንዲሁም በሴቶች ላይ የተፈፀመ መገለል ነው ብለዋል።
በኬንያ ህገ መንግሥት መሰረት አንደኛው ፆታ ከሌላው በበለጠ ከ2/3 ኛውን የፓርላማ ወንበሮች መያዝ አይችልም ይላል።
ሆኖም ኬንያ ካሏት 350 የፓርላማ ወንበሮች መካከል 116 ወይም ከዚያ በላይ በሴቶች መያዝ ቢኖርበትም ቁጥራቸው ከዚያ ያነሰ ነው።
ፓርላማው "በህገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የስርዓተ ፆታ ስብጥር ለማስከበር ችላ ብሎታል፤ በተደጋጋሚም ይህንን ህግ እንዲያከብር የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቀርቦለት ነበር" በማለት ዳኛ ዴቪድ ደብዳቤው ላይ አስፍረዋል።
ፕሬዚዳንቱ ፓርላማውን እንዲበትኑት የማማከር ህጋዊ ግዴታም እንዳለባቸውም ጠቅሰዋል።
የፓርላማ ቃለ አቀባይ ጀስቲን ሙቱሪ በበኩላቸው ፓርላማውን መበተን የማይጨበጥ ነው ብለውታል።
ከአስር አመት በፊት በፀደቀው አዲሱ የኬንያ ህግ መሰረት 2/3ኛ የፆታ ስብጥር ስርአት ህግ በአምስት አመታቱ የፓርላማ ቆይታ ሊከበር ይገባል ይላል።
በወንዶች የተሞላው የኬንያ ፓርላማ የሴቶችን ቁጥር ለመጨመር ምን ማድረግ አለበት የሚለው አወዛጋቢም ሆኗል።












