እንግሊዝ፡ በሚንቀሳቀስ መኪና ላይ ቪዲዮ ለመቅረፅ በመስኮት የወጣችው ግለሰብ ወደቀች

ኤም 25 የተባለው ጎዳና

የፎቶው ባለመብት, Google

ታትሟል

በእንግሊዟ ዋና መዲና ለንደን ውስጥ ነው ጉዳዩ የተከሰተው፤ እየሄደ ባለ መኪና ቪዲዮ ለመቅረፅ በመስኮት የወጣችው ግለሰብ መውደቋ ተነግሯል።

ግለሰቧ የማህበራዊ ሚዲያ ለሆነው ስናፕ ቻት ስትቀርፅም እንደነበር ተጠቅሷል።

ከመኪናው የወደቀችውም በትናንትናው ዕለት መሆኑንም የትራፊክ ፖሊስ ትዊተር በገፁ አስፍሯል።

ግለሰቧ ክፉኛ እንዳልተጎዳች የተገለፀ ሲሆን ፖሊስ እድለኛም ናት ብሏል " ክፉኛ አልተጎዳችም፤ ልትሞት ትችል" ነበር በማለት ሊሆን ይችል የነበረውን ጠቁሟል።

በቦታው የደረሱ የህክምና ባለሞያዎች አክመዋታል። እስካሁንም በቁጥጥር ስር የዋለ ሰው እንደሌለም ፖሊስ አስታውቋል።

የፎቶ እና የተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ) መልዕክቶችን ለመለዋወጥ የሚያስችለው ስናፕቻት በተለይም ሰዎች የሚገኙበትን ወቅታዊ ሁኔታ እና ውሏቸው ምን እንደሚመስል ለቅርብ ጓደኞች፣ ወዳጆች እንዲሁም ቤተሰቦችን ለማስቃኘት በርካቶች ተመራጭ ያደርጉታል።

የትራፊክ ፖሊስ በትዊተር ገፁ ላይ እንዳሰፈረው የፊት ወንበሩ ወደፊት ተጠግቶ ሰውነቷን በመስኮት በኪል አውጥታ ቪዲዮ ስትቀርፅ እንደነበርና ኤም 25 በተባለው የለንደን ጎዳናም ላይ መውደቋም ተጠቅሷል።

"ክፉኛ ልትጎዳም ሆነ ልትሞት ትችል ነበር፤ በእድል ነው የተረፈችው" ብሏል።

የፖሊስ ቃለ አቀባይ በበኩላቸው ሜ25 ጎዳና ላይ ከሌሊቱ 1 ሰዓት 30 ላይ አንዲት ግለሰብ ከሚሄድ መኪና መውደቋ ሪፖርት እንደተደረገም በስፍራው መድረሳቸውን ገልፀዋል።

የደረሰባት ጉዳትም ህይወቷን አደጋ ላይ የሚጥል እንዳልሆነም ተገልጿል።