እግር ኳስ ፡ የአውስትራሊያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ማልያ በልካቸው አለመሰፋቱ ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአውስትራሊያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች የቡድኑ ማልያ በሴቶች ልክ የለም መባሉን ተከትሎ ቁጣቸውን እያሰሙ ነው።
የብሔራዊ ቡድኗ ከሜዳ ውጭ የምትጫወትበት ማልያ በአዲስ መልክ ቢሰራም ለሴቶች የሚሆን የለም ተብለዋል ደጋፊዎች።
መቶ በመቶ ከፖሊስተር ጨርቅ የተሠራው አዲሱ ማልያ ባለፈው አርብ ከወንዶቹ ማልያ ጋር ነበር ለገበያ የቀረበው።
ነገር ግን የሴቶች ብሔራዊ ቡድኗ በትዊትር ገጿ እንዳስታወቀችው አዲሱ ማልያ በሴቶች ልክ አልተሰራም፤ በወንዶች እንጂ በማለት ያጋጠመውን ችግር ገልጸዋል።
'ማቲልዳስ' በተሰኘ ቅፅል ስም የምትታወቀው ቡድን ይፋ እንዳደረገችው አዲሱ ማልያ እስከ 2022 [በአውሮፓውያኑ] ድረስ በሴቶች ልክ አይሠራም።
የአውስትራሊያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዓለም ሰባተኛ ናት።
የአውስትራሊያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ናይኪ የተሰኘው የስፖርት አልባሳት አምራች ያመረቱት አዲሱ ቢጫ ማልያ ገበያ ላይ ፈላጊው በዝቷል።
ነገር ግን ማልያው በሴቶች ልክ ባለመሠራቱ ሴቶቹም የሚለብሱት ለወንዶቹ የተሠራውን ነው ተብሏል።
ምንም እንኳ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን አባላት ማልያውን ለብሰው ፎቶ በመነሳት ማስታወቂያ ቢሰሩም ደጋፊዎች ግን ይህ አላስደሰታቸውም።
ብሔራዊ ቡድኗ ችግሩ የሚቀረፈው በአውሮፓውያኑ 2022 አዲስ ማልያ ሲተዋወቅ ነው ብላለች።
ደጋፊዎችን ጨምሮ የብሔራዊ ቡድኑ አባላት በሁኔታው የተሰማቸውን ቅሬታ በማኅበራዊ ድር አምባ ገፆቻቸው ላይ ገልፀዋል።
አውስትራሊያ 2023 ላይ የሚካሄደውን የሴቶች ዓለም ዋንጫ ታዘጋጃለች።
የአገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አፈ ቀላጤ ስለጉዳዩ በአንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ ተጠይቀው "ተጨማሪ አስተያየት መስጠት አልችልም" ብለዋል።
የአውስትራሊያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን 'ማቲልዳስ' አባላት በአውሮፓውያኑ 2019 ከወንዶቹ እኩል ደመወዝ እንዲከፈላቸው መወሰኑ ይታወሳል።
በስምምነቱ መሠረት ሁለቱም ብሔራዊ ቡድኖች እኩል ደመወዝና የማስታወቂያ ገቢ ያገኛሉ።
አልፎም በአውሮፕላን ሲጓዙ የሚደርግላቸው እንክብካቤና የልምምድ ሜዳ ቁሳቁስ አቅርቦት ከወንዶቹ እኩል እንዲሆን ሆኗል።
ነገር ግን አሁንም ወንዶቹ በሚወዳደሩባቸው ውድድሮች ካሸነፉ እንዲሁም ዋንጫ ካገኙ ከሴቶቹ የተሻለ ገንዘብ ያገኛሉ።
የወንዶቹ ብሔራዊ ቡድን በዓለም 41ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
















