ዶናልድ ትራምፕ፡ የአሜሪካው ፕሬዚደንት የቀረበባቸውን የወሲባዊ ትንኮሳ ክስ ተቃወሙ

ታትሟል

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በጎርጎሮሳዊያኑ 1997 በኒው ዮርክ የቀድሞዋ ሞዴል ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ፈፅመዋል በሚል የቀረበባቸውን ክስ ተቃወሙ።

የቀድሞዋ ሞዴል አሚ ዶሪስ ትባላለች። ትንኮሳው የደረሰባትን ሁኔታ እንዲህ ታስረዳለች።

"አሜሪካ የቴኒስ ውድድር በምታካሂድበት ወቅት ውድድሩን ለመመልከት ስታዲየም ገብቼ ነበር። የተቀመጥኩትም ከቀድሞ ፍቅረኛየ ጃሰን ቢን ጋር ትራምፕ በሚገኝበት የታላላቅ ሰዎች መቀመጫ [ቪ.አይ.ፒ] ቦታ ነበር።

ከዚያም ወደ መታጠቢያ ቤት ሄድኩ። ከመታጠቢያ ቤቱ ስወጣ ትራምፕ ደጅ ላይ እየጠበቀኝ ነበር። አስገድዶ ሊስመኝ ሲሞክር ከላየ ላይ ገፈተርኩት። ከዚያ በእጁ አጥብቆ ያዘኝ፤ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቸን፤ መቀመጫየን፣ ጡቶቼን፣ ጀርባየን ሁሉንም ሰውነቴን መዳሰስ ጀመረ፤ አስገድዶም ሳመኝ" ስትል ነበር ለዩናይትድ ኪንግደሙ ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ የተፈጠረውን ያስረዳችው።

ዶሪስ በወቅቱ የ24 ኣመት ወጣት ነበረች። በርግጥ ያ ሁሉ ሲፈፀምባት ዝምታን አልመረጠችም።

"በእጁ ውስጥ ስለነበርኩ ራሴን ማላቀቅ አልቻልኩም ነበር" ብላለች። ለትራምፕም ድርጊታቸውን እንዲያቆሙ ወትውታቸዋለች። ግን "የእኔን ውትወታ ከእቁብም አልቆጠረው" ብላለች።

ዶሪስ ይህንን ታሪኳን አደባባይ ማውጣት የፈለገቸው ለሁለት ታዳጊ ሴት ልጆቿ አርአያ ለመሆን እንደሆነ ተናግራለች።

ይህንን ታሪክ ከአራት ዓመታት በፊት ለመናገር አስባ የነበረ ቢሆንም፤ ለቤተሰቦቿ በመፍራት ዝምታን መርጣ ቆይታለች።

የትራምፕ ጠበቃ ግን የቀረበውን ክስ "ደንበኛየ የተባለውን አልፈፀመም" ሲሉ ተቃውመውታል። ክሱንም "ከምርጫው በፊት እርሱን ለማጥቃት የተደረገ ሙከራ ነው" ብለውታል።

ፕሬዚደንቱን በወሲባዊ ትንኮሳ ወንጀል የከሰሰችው ዶሪስ ብቻ አይደለችም። በርካታ ሴቶች ናቸው። ይሁን እንጅ ፕሬዚደንቱ የቀረበባቸውን ሁሉንም ክሶች ተቃውመዋል።

የትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ሕጋዊ አማካሪ ጀና ኢሊስ በበኩላቸው፤ የቀረበው ክስ "ሙሉ ለሙሉ ከእውነት የራቀ ነው" ሲሉ ለሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።

አክለውም "አንድን አካል ለመጉዳት ይህንን 'እርባና ቢስ' ታሪክ ያወጣውን ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ ተጠያቂ ለማድረግም ማንኛውንም የሕግ አግባብ እንጠቀማለን" ብለዋል።

የትራምፕ ጠበቃም ለዘ ጋርዲያን ሲናገሩ፤ ለቀረበው ክስ "ሌሎች እማኞች ሊኖሩ ይገባ ነበር" በማለት፤ ክሱ በመጭው ሕዳር ወር የሚካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ፖለቲካዊ ሊሆን ይችላል" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ጠበቃው አክለውም በወቅቱ ነበር የተባለው የቀድሞ ፍቅረኛዋ ቢን፤ ዶሪስ "በወቅቱ ያልተመቻት ወይም ልክ ያልሆነ ነገር እንዳለ እንደነገረችው እንደማያስታውስ" ተናግሯልም ብለዋል።

ፕሬዚደንት ትራምፕ ላይ የወሲባዊ ትንኮሳ ክስ ሲቀርብባቸው የመጀመሪያው አይደለም ።

ከአራት ዓመታት በፊት በተካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ትራምፕ ከወሲባዊ ትንኮሳ ጋር በተያያዘ በርካታ ክሶች ቀርበውባቸዋል። ይህም ሴቶች የጎሪጥ እንዲመለከቷቸው እንዳደረጋቸው ይነገራል።

በርካታ ክስ አቅራቢዎችም ወደፊት መምጣት የጀመሩት፤ ትራምፕ እንደ እርሳቸው ያሉ ዝነኞች 'ሴቶች ላይ ምንም ነገር ማድረግ ይችላሉ' ሲሉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ከወጣ በኋላ ነበር።

የወሲባዊ ትንኮሳ ክስ ካቀረቡት መካከልም አሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ ጂን ኢ ካሮል አንዷ ስትሆን ትራምፕ በጎርጎሮሳዊያኑ 1995 መጨረሻ ወይም 1996 መጀመሪያ ላይ በቢሮዋ ወሲባዊ ትንኮሳ እንዳደረሱባት ነበር ክስ ያቀረበችው።

ትራምፕ ግን ክሱን 'ሀሰት ነው" ብለዋል።